የድንበር የለሾች ሐኪሞች ቡድን ለአላማጣ አጠቃላይ ሆስፒታል የሚያደርገውን ድጋፍ ማስፋቱን ተናገረ

የድንበር የለሾች ሐኪሞች ቡድን (MSF) በአላማጣ አጠቃላይ ሆስፒታል የሚሰጡ አጣዳፊ የሕክምና አገልግሎቶችን ለማጠናከር እና ለማደስ የሚያደርገውን ድጋፍ ማስፋፋቱን አስታወቀ።

ሆስፒታሉ ለአላማጣ ከተማና አካባቢዋ ለሚገኙ ወደ 300,000 የሚጠጉ ነዋሪዎች ዋና የሕክምና ማዕከል ቢሆንም፣ በመድኃኒትና ቁሳቁስ እጥረት፣ በሰው ኃይል እጥረት እንዲሁም በውሃና ኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት መጎዳት ምክንያት አገልግሎት ለመስጠት ተቸግሮ ቆይቷል።

ድጋፉ በዋናነት የእናቶች ሕክምና፣ የአደጋ ጊዜ ሕክምና እና አዲስ የተወለዱ ሕፃናት የፅኑ ሕክምና ክፍሎች ላይ ያተኮረ ነው።

የመሰረተ ልማት ጥገና፣ አስፈላጊ የሕክምና ቁሳቁሶችን ማቅረብ፣ ለጤና ባለሙያዎች የሥራ ላይ ሥልጠና መስጠት እና የሪፈራል (የታካሚዎች ዝውውር) ሥርዓቱን ማጠናከር ይገኙበታል ሲል ለጣቢያችን በላከው መግለጫ አሳውቋል።

ይህ ድጋፊ በሕክምና አገልግሎት እጥረት ምክንያት የሚከሰቱ የሰዎች፣ የእናቶችና የሕፃናትን ሞቶችን መቀነስ ዋነኛ አላማው መሆኑን ገልጻል።

«እነዚህ ክፍሎች ፈጣንና ጥራት ያለው ሕክምና ካላገኙ የፀኑ ታካሚዎች ለሞት የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ የሆኑባቸው ክፍሎች ናቸው።» ብለዋል ፋራይ ማሩሜ የMSF የፕሮጀክት ሕክምና አስተባባሪ፡፡

የድንበር የለሾች ሐኪሞች ቡድን እ.ኤ.አ. ከ2023 ጀምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበሩ ችግሮች ምክንያት የተጎዳውን የጤና ሥርዓት ለማገዝ እየሰራ ሲሆን፣ በኮሬም አጠቃላይ ሆስፒታል እና በተንቀሳቃሽ የሕክምና ቡድኖች አማካኝነት የሕክምና አገልግሎቶችን በነጻ ሲሰጥ ቆይቷል። አሁን ለአላማጣ ሆስፒታል የተደረገው ማስፋፊያ የነዋሪዎችን ሕክምና የማግኘት ዕድል የበለጠ ያጎለብታል ተብሏል።

ሐምሌ 28/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *