ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የባህር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱን ተርሚናል በዛሬው ዕለት መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃው ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ አውሮፕላን ማረፊያው ለኢትዮጵያ ቁልፍ የበረራ በሮች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዚህ አዲስ ተርሚናል መጠናቀቅ ለከተማዋም ሆነ ለሀገሪቱ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ከዘመናዊ ተርሚናል ግንባታ ባለፈ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባህር ዳር በቅርብ ጊዜያት ካስተናገደቻቸው ፈተናዎች ማግስት የዚህ ተርሚናል ተጠናቆ አገልግሎት መጀመሩ የፅናት፣ የማገገምና ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት ማረጋገጫ መሆኑን አስረድተዋል።
የአዲሱ ተርሚናል ሰፊ የአውሮፕላን ማቆሚያዎችን፣ የላቁ መሰረተ ልማቶችን፣ የተስተካከሉ መዳረሻ መንገዶችን እና ዘመናዊ መገልገያዎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጻል፡፡
የአውሮፕላን ማረፊያውን የመቀበል አቅም በማሳደግ የአካባቢውን እያደገ የመጣ የጉዞ ፍላጎት የሚያሟላ ሲሆን፤ ለመንገደኞችም ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል።
አዲሱ ተርሚናል ከተማዋን እያደገ ካለው የከተማ ትራንስፎርሜሽን ጋር ተዳምሮ ባህር ዳርን ለዓለም አቀፍ እና ለሀገር ውስጥ በረራዎች ሌላኛዋ ቁልፍ መዳረሻና ማዕከል ያደርጋታል ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባህር ዳርን የመሰለች ንቁ ከተማ የምታስገኘውን ሙሉ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አምቆ ለማውጣትና ለማረጋገጥ የአካባቢው ማህበረሰብ ሰላሙን አጠናክሮ መጠበቁን እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ሐምሌ 30/2018 ዓ›ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የባህር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲስ ተርሚናል መረቁ
