የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከታቀዱት ስራዎች መካከል ሶስት አራተኛ ያህሉን ማጠናቀቁን ገለጸ

ኮሚሽኑ ዛሬ በሰጠው መግለጫ፤ ለረጅም ጊዜ ሲደከምበት የቆየው የዚህ የምክክር ሂደት ውጤት በቅርቡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ እንደሚሆንና አብዛኛው የዝግጅትና የውይይት ስራ በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቁን ገልጿል።

በሂደቱ ላይ ስለሚነሱ ቅሬታዎች በተመለከተም፤ አንዳንድ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸውን ቅሬታዎች በተዘረጋው የቅሬታ መፍቻ ስነ-ስርዓት መሠረት በጥንቃቄ እየተመለከተ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ አክሎም “በውይይቱ ሂደት ውስጥ አለመግባባቶችና ግጭቶች መኖራቸው አልተካደም፤ ይሁን እንጂ እነዚህ አለመግባባቶች መኖራቸው የሀገራዊ ምክክሩን አስፈላጊነት ይበልጥ የሚያጎላው ነው” ብሏል።

አክሎም ልዩነቶቹ በውይይትና በመደማመጥ ተፈትተው ወደ ጋራ መግባባት መደረሱ ለሂደቱ ስኬታማነት ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጿል።

በትላንትናው ዕለት እናት ፓርቲ እና አብን የጉባኤው ሂደት የገዢው ፓርቲን ፍላጎት ለማስፈጸም ያለመ እንቅስቃሴ እየተደረገበት ነው ሲሉ ቅሬታ አቅርበው ነበር።

አብን ጉባኤው ከተጀመረ በኋላ አዳዲስ ተመካካሪዎች ግልጽ ባልሆነ መንገድ መጨመራቸውንና የገዥው ፓርቲ አመራሮች በተለያዩ የሥራ ቡድኖች እየገቡ ጫና መፍጠራቸውን ተቃውሟል። ኮሚሽኑ በታዩ ግድፈቶች ላይ አፋጣኝ ማስተካከያ ካላደረገም ራሱን ከጉባኤው እንደሚያገል ማስጠንቀቁ ይታወሳል።

እናት ፓርቲ በበኩሉ፤ በምክክሩ ላይ አብላጫውን ቁጥር የያዙት የገዥው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች በመሆናቸው ሂደቱ “ቀድሞ የተወሰነ ውሳኔን ቅቡልነት እንዲኖረው የማድረግ ሥራ ነው” ሲል አጣጥሎታል።

በተጨማሪም ጉባኤው ኢትዮጵያን ለማጽናት ሳይሆን ዋና ዋና መገለጫዎቿ ለድርድር የቀረበበት መድረክ ሆኗል ሲል ከሷል።

ለዓለም አሰፋ

ነሐሴ 07/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *