በግምታዊ ግብር አጣጣል ሂደት የግብር ከፋዮች ከልክ በላይ ግብር ሊጣልባቸው እንደሚችል የሕግ ባለሙያዉ አቶ ዮሴፍ ወርቀልኡል ገልጸዋል።
አቶ ዮሴፍ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በግምታዊ ግብር አጣጣል ሂደት የግብር ከፋዩ የመስሪያ ቦታ፣ አካባቢው እና የቤቱ ስፋት ታይቶ ግብር የሚጣልበት ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት ይህ ነው ተብሎ የሚቀርብ የሰነድም ሆነ ሌሎች ማስረጃዎች ባለመኖራቸው፤ ግብር ከፋዮች ከልክ በላይ የሆነ ግብር ሊጣልባቸው እንደሚችልም አቶ ዮሴፍ ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም የግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤት ማግኘት ያለበትን ገቢ ላያገኝ እንደሚችል አንስተዋል።
ይሁን እንጂ የግብር ከፋዩን ትክክለኛ ገቢ የሚያሳይ የሂሳብ መዝገብ ወይም ሌላ ተጨባጭ ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ የሚደረግ ግምት ለስህተት ተጋላጭ በመሆኑ ከልክ በላይ ግብር ሊጣል እንደሚችል አቶ ዮሴፍ ገልጸዋል።
ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤የቀን ገቢ ግምት በዘፈቀደ የሚወሰን እንዳልሆነ እና እንደ እርሳቸው ገለጻ የንግዱ ዘርፍ፣ የንግድ ቦታው የሚገኝበት አካባቢ፣የቦታው ስፋት፣ በአካባቢው በተመሳሳይ ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎች እና የሚይዟቸው ዕቃዎች ዋጋ ታይተው ግምቱ እንደሚሰላ አንስተዋል።
አቶ ሰውነት እንደገለጹት፤የደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች ዓመታዊ ሽያጫቸው ከ2 ሚሊየን ብር በታች ሲሆን፤እነዚህም ግብር ከፋዮች የሂሳብ መዝገብ እንዲይዙ እንደማይገደዱም እና የቀን ገቢ ግምት እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል። ይህም በተጨማሪ የገበያ ዋጋ ጥናት ተካሂዶ እንደሚፈጸም ገልጸዋል።
አቶ ሰውነት አክለውም በተመሳሳይ የንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች የተለያየ የቀን ገቢ ግምት ሊደረግላቸው እንደሚችልም እና ይህም ከንግድ ቦታው አካባቢ እና ከቦታው ስፋት አንጻር እንደሚወሰን አብራርተዋል።
በግምታዊ ግብር አሰባሰብ ሂደቱ ላይ ቅሬታ ያለው ግብር ከፋይ በተቀመጠው የይግባኝ አቀራረብ ሂደት መሠረት ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችል አቶ ሰውነት ገልጸዋል።
በመሆኑም የግምታዊ ግብር አሰባሰብ ሂደቱ በተጨባጭ መረጃና ጥናት እንዲደገፍ፣ ግብር ከፋዮችም የሂሳብ መዝገብ በመያዝ ትክክለኛ ገቢያቸውን ማሳየት የሂደቱን ፍትሐዊነት ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑ ተጠቁሟል።
ሰላማዊት ዲታ
ነሐሴ 08/2018 ዓ.ም
