በኢትዮጵያ የፅሁፍ ቅርሶችን የማስመዝገብ ሂደት ከተቋረጠ ሀያ አመታት ተቆጥሯል።
በመጪዉ አመት ታህሳስ ወር በአለም ቅርስ መዝጋቢዉ ድርጅት (ዩኔስኮ) ለመመዝገብ የሚያስችል ምዕራፍ ላይ ያሉ ሁለት ጥንታዊ የፅሁፍ ቅርሶች መኖራቸዉ ተገልፆል።
እነዚህ ፅሁፎች በወንጌል ላይ የሚገኝ እንዲሁም ሀረር ላይ የተገኙ ጥንታዊ ፅሁፎች ስለመሆናቸውም ተነግሯል።
በባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዩች ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ጌታነህ ገዛኸኝ እንደሚገልጹት ፤ በባለፈዉ አመት የቅርስ መግለጫ የተዘጋጀላቸዉ ጥንታዊ ፅሁፎች ለቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን እንደቀረበለት ገልፀዋል።
አቶ ጌታነህ ባለስልጣኑ ከቀረቡለት ዉስጥ እነዚህን ሁለቱን በመምረጥ ለዩኔስኮ መላኩን ተናግረዋል።
ለመመዝገብ ጫፍ ደርሰዋል በተባሉት በእነዚህ ሁለት ጥንታዊ ፅሁፎች ላይ ከየትኛውም አገር የይገባኛል ጥያቄ አለመነሳቱን ተከትሎ ዩኔስኮ በይፋ ለቅርስነት ሊመዘግባቸዉ መቃረቡን አቶ ጌታነህ ነግረውናል።
ሌሎች አስር የጥንታዊ ፅሁፎች መግለጫ እየተዘጋጀላቸው መሆኑን የነገሩን ባለሙያዉ በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው የፅሁፍ ቅርስ አስመዝጋቢ ኮሚቴ በእጩነት ሊቀርቡ የሚችሉትን የመለየት ስራ ያለበት ነዉ።
ከሀያ አመት በፊት የተመዘገቡ አስራ ሁለት ብቻ የፅሁፍ ቅርሶች በአለም የትዉስታ ማህደር ተመዝግበው የሚገኙ እንደሆነ ይገለፃል ።
አብዛኞቹ ተመዝግበዋል የተባሉ የፅሁፍ ቅርሶች የነገሥታት ደብዳቤዎች እና ጦማሮች ሲሆኑ፤ ዘመናቸዉ ከ19ኛዉ እና 20ኛዉ ክፍለዘመን የተሻገሩ አይደሉም።
ከዚህ ዉስጥ መፅሀፈ ፍትሐ ነገስት፥ መፅሀፈ ግብረ ህማማት እንዲሁም የአጼ ቴዎድሮስ ለእንግሊዝ ንግስት ቪክቶሪያ የጻፉት ደብዳቤ ይገኙበታል።
ቁምነገር አየለ
ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም
