ቴህራን በቂ የውጭ ምንዛሬ አላት ሲሉ የኢራን ማዕከላዊ ባንክ ገዢ ለትራምፕ ተናገሩ

ማዕከላዊ ባንኩ 2 ቢሊየን ዶላር ወደ ምንዛሬ ገበያው ለማስገባት ዝግጁ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ምንም እንኳን የአሜሪካ ማዕቀብ እና የኢኮኖሚ ጫና ቢበረታም፤ኢራን በቂ የውጭ ምንዛሬ እንዳላት የማዕከላዊ ባንክ ገዢ አብዱልናስር ሄማቲ ተናግረዋል።

ተስኒም የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ማዕከላዊ ባንኩ 2 ቢሊየን ዶላር ወደ ውጭ ምንዛሬ ገበያው ለማስገባት ዝግጁ ነው።

የአሜሪካን የኢኮኖሚ ውድቀት ክስ ውድቅ ያደረጉት ሄማቲ፤ኢራን የውጭ ምንዛሬ ገቢዎችን እና ተከፋይ ሂሳቦችን መሰብሰቧን እንደቀጠለች ገልጸው፤ዝርዝራቸው ሊገለጽ የማይችል የአገር ውስጥ ክምችትና ሌሎች ሀብቶች እንዳሏትም ተናግረዋል።

የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሥርዓት በአዲሱ ማዕቀብ ውስጥም መስራቱን እንደቀጠለ የገለጹት ሄማቲ፤የሪያል ዋጋ በቅርቡ መውረድ በአብዛኛው ከሥነ-ልቦናዊ ሁኔታዎች ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢራን ወደ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ውስጥ ገብታለች የሚለውን ሀሳብ ውድቅ በማድረግ፤ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እና ሰፊ የኢኮኖሚ ጫና ቢኖርም ይህ የመከሰቱ ዕድል አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በጦርነቱ እና በአንዳንድ መሰረተ ልማቶች ላይ በደረሰው ውድመት ምክንያት የስራ አጥነት ቁጥር መጨመሩን ያመኑት ሄማቲ፤በሁለተኛው የኢራን ዓመት አጋማሽ ላይ ለአነስተኛ እና መካከለኛ ንግዶች የፋይናንስ ድጋፍ ቅድሚያ እንደሚሰጥ አክለዋል።

እነዚህ አስተያየቶች የተሰጡት የኢራን ሪያል ከአሜሪካ ዶላር ጋር ባለው ዋጋ ላይ አዲስ ተጽዕኖ እየገጠመው ባለበት እና በአሜሪካ-እስራኤል ጦርነት የኢኮኖሚ መዘዝ እንዲሁም በጠነከረው የአሜሪካ ማዕቀብ ወቅት ነው።

ዋሽንግተን በቅርቡ በቴህራን ላይ የምታደርገውን የኢኮኖሚ ጫና ዘመቻ ያሰፋች ሲሆን፤ ዋና ዋና የኢራን ገቢ ምንጮችን እና ዓለም አቀፍ ንግድን ኢላማ አድርጋለች።

ኢራን እና አሜሪካ በሰኔ ወር ጦርነቱን ለማቆም ያለመ ባለ 14 ነጥብ የመግባቢያ ስምምነት ቢፈራረሙም፤ ጊዜያዊ ስምምነቱ ግን በፍጥነት መፍረሱ ይታወሳል።

ሀና ሰይፉ

ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *