ደንበኞች ቴሌብርን አሁን ላይ ከጥቃቅን የገንዘብ ዝውውሮች በተጨማሪ ከፍ ላሉ ክፍያዎች ጭምር እየተጠቀሙ መሆናቸውን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገልፀዋል።
ከፍተኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ ባለበት ሁኔታ ደግሞ የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ዝውውር ገደብ መኖሩ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ኩባንያው ከደንበኞች ተደጋጋሚ ቅሬታ እንደደረሰው ተናግረዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ይህንን ያሉት ኢትዮ ቴሌኮም “የቀጣዩ አድማስ”የ3 ዓመት ስትራቴጂ 2ኛ ዓመት የስራ ዕቅዱን ለጋዜጠኞች ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው።
ዕቅዱ የደንበኞችን ቁጥር ከማሳደግ ባሻገር የኔትወርክና የአገልግሎት ጥራትን ማሳደግ ዋነኛ ግቡ ማድረጉን ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።
ከተያዙት ዕቅዶች መካከል የቴሌብር ደንበኞቹን ቁጥር ከ67 ሚሊየን በላይ ማድረስ አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።
በቴሌብር የሚደረግ የገንዘብ ዝውውር መጠንን ደግሞ ወደ 7.40 ትሪሊየን ብር ለማሳደግ መታቀዱንም ፍሬሕይወት ታምሩ ተናግረዋል።
ቴሌብር ስራ ከጀመረበት በእነዚህ 5 ዓመታት ውስጥ 9 ትሪሊየን ብር የገንዘብ ዝውውር ተካሂዶበታል ያሉ ሲሆን፥ በዚህኛው ዕቅድ ግን በአንድ ዓመት ውስጥ 7.4 ትሪሊየን ብር ለማዘዋወር መታቀዱን አንስተዋል።
በዚህ ዓመት ከተገኘው 2መቶ15 ቢሊየን ብር ገቢ በ2019 በጀት ዓመት 2መቶ 95 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል።
ለኩባንያው ገቢ የዳታ እና ኢንተርኔት አገልግሎት ከፍተኛውን ቦታ መያዛቸው የተነሳ ሲሆን፥ በቀጣይ ለተያዘው ዕቅድም ከፍተኛውን ቦታ የሚይዝ መሆኑ ተገልጿል።
አጠቃላይ የደንበኞቹን ቁጥር ወደ 96.2 ሚሊየን ለማሳደግ ዕቅድ መያዙንም ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።
እስከዳር ግርማ
ነሐሴ 28/2018 ዓ.ም
