አሚጎስ የቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ ህብረት ስራ ማህበር በህብረት ስራ ማህበራት ዘርፍ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ከወረቀት ንክኪ የጸዳ የስማርት አገልግሎት ማዕከል በዛሬው ዕለት በይፋ አስመረቀ።
የፌዴራል ፈቃድ አግኝቶ የክልል ከተሞችን ጨምሮ 28 ቅርንጫፍ ቢሮዎችን የከፈተው ተቋሙ፣ በቀጣይ ወራት ተጨማሪ 23 ብራንቾችን ለመክፈት አቅዶ እየሰራ ይገኛል ተብሏል ። የሀብት መጠኑን ወደ 10 ቢሊዮን ብር በማሳደግ የእድገት ደረጃውን ከፍ እያደረገ የሚገኘው ማህበሩ፤ ላለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ከ50 በመቶ በላይ ትርፍ ለባለአክሲዮን አባላቱ ማከፋፈሉ አስታውቋል
ከፋይናንስ አገልግሎቱ ጎን ለጎን በከተማ ልማት እና በበጎ አድራጎት ስራዎች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ የሚገኘው አሚጎስ፣ በራሱ ሰራተኞች የተሰሩ የሞባይል መተግበሪያዎችን በመጠቀም ዲጂታል አሰራሮችን ዘርግቷል።
አገልግሎቶቹን ከንግድ ባንክ ጋር ያቀናጀው ማህበሩ፣ በቀጣይ ከቴሌብር እና ከአዋሽ ባንክ ጋር አዳዲስ አገልግሎቶችን ለማስጀመር በሂደት ላይ መሆኑን ገልጿል።
በዛሬው ዕለት የተመረቀው አዲስ የስማርት አገልግሎት ማዕከልም ይህንን የቴክኖሎጂ ሽግግር ወደሚቀጥለው ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው ተብሎል ። ማዕከሉ አባላት የአባልነት ምዝገባ፣ የኢንፎርሜሽን ጥያቄዎች፣ የብድር ሂደት ክትትል እና የሰነድ ማሟላት ስራዎችን ከወረቀት ንክኪ ነፃ በሆነ መልኩ በስማርት መገልገያዎች ፈጣንና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ የሚያከናውኑበትን ዘመናዊ አሰራር ይዞ መጥቷል።
አቤል እስጢፋኖስ
መስከረም 12/2019 ዓ.ም
