የእህቱን ማንነት በመጠቀም ለ8 ዓመታት እንደ ሴት ሲኖር የነበረው ወንጀለኛ በኢስታንቡል ተይዟል።
እ.ኤ.አ. ከ2018 ጀምሮ ከሕግ አምልጦ ሲፈለግ የነበረው ቱግሩል ባሻር የተባለ የቱርክ ዜጋ፣ ሙሉ በሙሉ ገጽታውን በመቀየር እና የእህቱን ማንነት በመጠቀም ለዓመታት እንደ ሴት ሲኖር ቆይቶ በቁጥጥር ስር መዋሉን የሀገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል።
ተከሳሹ እ.ኤ.አ. በ2010 የመንግሥት ባለሥልጣን መስሎ በመቅረብ በፈጸማቸው ሦስት የዝርፊያ ወንጀሎች የሦስት ዓመት የእስራት ፍርድ ተበይኖበት የነበረ ቢሆንም፣ ፍርዱን ሳይጨርስ በ2018 ከሕግ አምልጦ ሸሽቶ እንደነበር ተገልጿል።
የኢስታንቡል ፖሊስ ባካሄደው ልዩ ምርመራም፣ ወንጀለኛው በከተማዋ በሚገኘው ካዲኮይ በተባለ አካባቢ ይኖር እንደነበር ታውቋል።
መርማሪዎች እንደገለጹት ከሆነ፣ የወንጀለኛው የገጽታ ለውጥ እጅግ ስር ነቀል በመሆኑ በቆዩ የፖሊስ መዝገብ ፎቶዎች ብቻ መለየት አልተቻለም ነበር፤ በዚህም ምክንያት በቤተሰቦቹ ላይ ጥብቅ ክትትል ሲደረግ ቆይቷል።
በዚህ ክትትል በእህቱ መኖሪያ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ሴቶች አንድ ዓይነት የመታወቂያ ካርድ ተራ በተራ እንደሚጠቀሙ በመረጋገጡ፣ ፖሊስ ባካሄደው ድንገተኛ ፍተሻ ተከሳሹን በእህቱ መታወቂያ ሲጠቀም እጅ ከፍንጅ ይዞታል።
ምንም እንኳን ገጽታው ሙሉ በሙሉ የተቀየረ ቢሆንም፣ የተደረገው የጣት አሻራ ምርመራ እውነተኛ ማንነቱን እንዳረጋገጠው ተጠቅሷል።
የቱርክ የደህንነት ባለሥልጣናት እንዳረጋገጡት፣ ተከሳሹ በሲቪል ምዝገባ ስርዓት ውስጥ ጾታውን በይፋ ስላላሻሻለ፣ የአካል ገጽታ ለውጥ አድርጎ ቢገኝም ተበይኖበት የነበረውን የእስራት ፍርድ በወንዶች እስር ቤት ያጠናቅቃል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።
ሀመረ ፍሬው
መስከረም 12/2019 ዓ.ም
