የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላለፉት 16 ዓመታት ሲሰራበት በነበረው አሰራር ይስተዋሉ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶችንና የአሰራር ክፍተቶችን ለመቅረፍ፣ አዲስ የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ አጽድቆ ወደ ሥራ አስገብቷል።
በአዲሱ አዋጅ ቁጥር 92/2018 መሠረት፤ ቀደም ሲል በነበረው አሰራር በከተማዋ የልማት ድርጅቶች ላይ ይፈጠር የነበረውን የቁጥጥር ክፍተት ለማረም፣ ድርጅቶቹ ተገቢው ክትትልና ተጠያቂነት እንዲሰፍንባቸው በህጉ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲካተቱ ተደርጓል።
ከዚህም ባሻገር በሰው ንክኪ ምክንያት የሚፈጠሩ የአሰራር ብልሹነቶችን ለማስቀረት፣ አጠቃላይ የግዥ ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክ (e-Procurement) ቴክኖሎጂ እንዲመራ የሚያስገድድ ድንጋጌ መካተቱ ታውቋል።
በ13 ምዕራፎችና በ83 አንቀጾች የተዋቀረው ይህ አዋጅ፤ የመንግሥት ገንዘብ ያላግባብ እንዳይባክን እና በግዥ ሂደት ውስጥ ሙሉ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።
ልዑል ወልዴ
መስከረም 20/2019 ዓ.ም
