የሶማሊያ አክቲቪስቶች የህፃናትን ያለእድሜ እና በግዳጅ የሚደረጉ ጋብቻዎችን ይፈቅዳል ባሏቸው የሀገሪቱ ህግጋት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡
ሀገሪቱ ተቀብላ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህግጋቶች የሚጣረሱ የሀገሪቱ ህግጋቶች ላይ ማሻሻያ የሚጠይቀው የፊርማ ማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን እስካሁን 6ሺ ሰዎች የድጋፍ ፊርማቸውን አኑረዋል ነው የተባለው፡፡
የሶማሊያ ፓርላማ በሀገሪቱ የሰብአዊ መብቶችን የሚጥሱ ፣ በህፃናት ላይ አካላዊ ጥቃትን የሚያረታቱ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንቅስቃሴን የሚገድቡ ህግጋቶች እንዲሻሻሉ ድምፅ ሊሰጥ ይገባል የሚል ፅፉፍ በድጋፍ ማሰባሰቢ ሰነዱ ላይ ሰፍሯልም ተብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታ ድርጅትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትም የሀገሪቱ ህግጋት ላይ ትችት ሲያቀርቡ ከርመዋል፡፡
አክቲቪስቶቹ እንደሚናገሩት በሶማሊያ የወሲብ ጥቃት እየተስፋፋ ነው፡፡ ነገር ግን ተጎጂዎች ብዙውን ጊዜ በስውር እና በባህላዊ ድርጊቶች የተነሳ ቅሬታ ለማቅረብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፤ አሁን ግን ይሄ ተግባር መቆም ይኖርበታል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በያይኔአበባ ሻምበል
ነሀሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም
