ኢትዮጵያ በቀጣይ አመት በአዲስ አበባ ለሚካሄደው የአለም አቀፍ የቴሌኮሙኔኬሽን ልማት ጉባኤ ዝግጅት አህጉራዊ ስብሰባዎችን እንድትመራ መመረጧን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታዉቋል።
ለጉባኤው ስኬት ኢትዮጵያ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገች ሲሆን የጉባኤውን አህጉራዊ ስብሰባዎች በሊቀመንበርነት እንድትመራም ተመርጣለች።
ስብሰባውን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ የተመረጡት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር አህመዲን መሀመድ ለጉባኤው መሳካት ውጤታማ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል፡፡
በአህጉራት መከካል የሃሳብ ልውውጥ በማድረግ፣ ፍሬያማና ቀልጣፋ የዝግጅት ስራዎች እንዲከናወኑ ኢትዮጵያ ትሰራለች ያሉት ሊቀመንበሩ በኮቪድ ተፅዕኖ ውስጥ ስኬታማ ስራ ይሰራልም ተብሏል፡፡
የጉባኤው አስተናጋጅ ሀገር አህጉራዊ ስብሰባዎችን እንድትመራ መደረጓ ለኮንፈረንሱ የሚደረጉ ዝግጅቶች በፍጥነት እንዲከናወኑ እድል ይሰጣል ተብሎ ታምኖበታል።
ኢትዮጵያ 2021ንዱን የአለም አቀፍ የቴሌኮም ልማት ጉባኤ የምታስተናግድ ሲሆን ከተሳታፊ ሀገራት የቀረቡ ኮቪድ የደቀናቸው ስጋቶችን የተመለከቱ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማቅረቧንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታዉቋል፡፡
ከተለያዩ የአለም ሀገራት የተወጣጡ 250 ሰዎች የተሳተፉበት ስብሰባ በበይነ መረብ እንደተካሄደና፤ በኮቪድ 19 ምክንያት ጉባኤው በአካል ይካሄድ ወይንም በበይነ መረብ የሚሉት አማራጮች ላይ ሀገራት የተለያዩ ሃሳቦችን እያንፀባረቁ ነው።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
መጋቢት 02 ቀን 2013 ዓ.ም
