ኢትዮጲያን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም ሃገራት የአስትራዜኒካን ክትባት ለዜጎቻቸው መስጠታቸውን ቀጥለዋል፡፡
ይህንን የአስትራዜኒካን ክትባት መስጠቷንም እንደምትቀጥል ኢትዮጲያ አስታውቃለች፡፡
ሃገራችን ይሄ ክትባት በዓለም ጤና ድርጅት ውጤታማነቱ በመረጋገጡና እስካሁንም ክትባቱ የሚያስከትለው ጉዳት በትክክል ባለመረጋገጡ ኢትዮጲያ ለዜጎቿ ክትባቱን መሰጠቷን ትቀጥላለች ተብሏል፡፡
ነገር ግን ኢትዮ ኤፍኤም ዲኒማርክ ፣ፈረንሳይ፣ ጣልያንና ስፔይንን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት እያቋረጡት ያለውን ይህንን የአስትራዜኒካ ክትባት ሃገራችን እየሰጠችበት ያለችበት ሁኔታ ምን ይመስላል ? በክትባቱ ላይ የሚነሳውስ የደም መርጋት ችግር እንዴት ሊከሰት ይችል ይሆን ሲል በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሳንባና ፅኑ ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ ክሊኒካል አድቫይዘሪቲ አባል የሆኑትን ዶ/ር አስቻለው ወርቁን ጠይቋል፡፡
ዶ/ር አስቻለው እንደነገሩን በአሁኑ ወቅት ኢትዮጲያ እየሰጠች ያለችው መንግስት በመጀመሪያ ዙር ኮቫክስ ከተሰኘው ዓለም አቀፍ ጥምረት የተረከበውን 2 ነጥብ 2 ሚሊየን የአስትራዜኒካ ክትባትን ሲሆን ቀደም ብሎ በዚህ ክትባት ላይ እየተነሳ ያለው የደም መርጋት ችግር አጋጥሞናል ብለው ክትባቱን ካቋረጡ ሃገራትም በፊት የኮሮና ቫይረስ በራሱ የተያዙ አንዳንድ ሰዎች የደም መርጋት ችግር እንደሚያጋጥማቸው ነግረውናል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ ለህክምናው የደም ማቅጠን ሂደትን መከተል አንዱ የህክምናው መንገድ መሆኑን ሊታወቅ እንደሚገባ አስተውቀዋል፡፡
እንደ ዶ/ር አስቻለው ሃሳብ ከሆነ ማንኛውም መድሃኒት ጥቅም እንዳለው ሁሉ የጎንዮሽ ጉዳት ይኖረዋል፡፡
ነገር ግን የትኛውም መድሃኒት የሚያስከትለው ጉዳት ከየት ሊነሳ እንደቻለ ማጣራትን የሚጠይቅ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡
የክትባቱን የጎንዮሽ ጉዳት ለመለካት በተለይም የታካሚው የጤንነት ሁኔታ፤ በተፈጥሮ ማንኛውም ሰው ያለው በሽታን የመከላከል አቅምና ይህ ቫይረስ በራሱ የሚያስከትለው ጉዳት መመርመር እንደሚጠይቅ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ተዳምረው አሁን በክትባቱ ላይ የሚነሳው የጉዳት መጠን የተለየ እንዳልሆነ ሊታወቅ እንደሚገባ ነግረውናል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በቀጣይ በክትባቱ ላይ የሚያደርገውን ምርመራም በመከታተል በቀጣይ የሚወሰድ የተለየ መመሪያ ካለ ለህዝብ መረጃው ይፋ እንደሚደረግ፤ ይሁንና አሁንም ቢሆን ውጤታማነቱ በትክክል የተረጋገጠውን የአስትራዜኒካ ክትባት ዜጎች ያለምንም ጥርጣሬ ሊቀበሉት እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ አሁንም ቢሆን በክትባቱ ላይ ያለው ውጤታማነት በመረጋገጡ ሃገራት ክትባቱን መስጠት እንዳያቋርጡ አስታውቆ በክትባቱ ላይ የሚነሳውን ጥያቄ ለመመለስ በቀናት ውስጥ ምርመራን እንደሚያካሂድና በቀናት ውስጥም ውጤቱን ይፋ እንደሚደርግ አስታውቋል፡፡
እንደ ዶ/ር አስቻለው ሃሳብ ከሆነ ማንኛውም መድሃኒት ጥቅም እንዳለው ሁሉ የጎንዮሽ ጉዳት ይኖረዋል፡፡
ነገር ግን የትኛውም መድሃኒት የሚያስከትለው ጉዳት ከየት ሊነሳ እንደቻለ ማጣራትን የሚጠይቅ እንደሆነ ነግረውናል፡፡
በየዉልሰዉ ገዝሙ
መጋቢት 07 ቀን 2013 ዓ.ም
