በህዳሴ ግድብ ላይ የሚያተኩር አገራዊ የምሁራን ጉባኤ በጎንደር ዩንቨርሲቲ ሊካሄድ ነዉ፡፡

የጎንደር ዩንቨርሲቲ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደገለጸዉ፣ ወቅታዊዉን የህዳሴ ግድብ ግንባታና ዓለም አቀፍ የዉሃ ፖሊሲ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ጉባኤ ከሰኔ 3 እስከ 4 2013 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ አስታዉቋል፡፡

የዪንቨርሲቲዉፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ እንዳሉን ፤ጉባኤዉ የህዳሴ ግድብ እዉነታ፤ የአለም አቀፍ የዉሃ ፖሊሲና ህግ እንዲሁም የግጭት አፈታት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነዉ ብለዋል፡፡

በህዳሴዉ ግድብ ግንባታ ዙሪያ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረዉና ሉአላዊነት ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ፅሁፎችም በመድረኩ እንደሚቀርቡ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓባይ ምንጭ ብትሆንም ጉዳዩን በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ከማሳወቅ አንፃር ብዙ ክፍተት እንዳለ ያነሱት ዶክተር አስራት፤ በዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትኩረት ሰጥተዉ መስራት እንዳለባቸዉ ጠይቀዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ወጣቱ ትዉልድ ስለ ዓባይ ወንዝና ሥለ ህዳሴ ግድቡ እዉነታ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረዉ ለማስቻል ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ ትምህርት መሰጠት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድቡ ተጠቃሚ እንዳትሆን በርካታ ኃይሎች እየሰሩ እንደሚገኙ የገለፁት ፕሬዝዳንቱ፤ ግድቡ የህልዉናችንና የሉአላዊነታችን መገለጫ በመሆኑ መላዉ ኢትዮጵያዉያን በአንድነት መቆም እንዳለባቸዉም አሳስበዋል፡፡

በጉባኤዉ ላይ ከ ዉሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፤ ከሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር፤ ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸዉ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉም ታዉቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የግድቡ አጠቃላይ የግንባታ ሂደት 80 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን ሁለተኛዉ ዙር የዉሃ ሙሌትም በመጪዉ ክረምት እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
በአባቱ መረቀ
ሰኔ 01 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *