ህወሃት ሲሰራቸው የነበሩ አራት ግልፅ ሴራቸው

1/በስልጣን ላይ እያለ ከመከላከያ ጋር የሚስተካከል ተቋም ለመገንባት ያለመ ሰፊ ስራ ሰርቷል፡፡

2/ የቅጥረኝነትን ባህል አስፋፍቷል፤በየክልሉና በየቦታው ቅጥረኛን ሲያሰለጥን ሲያደራጅ ቆይቷል፤ዘርን ከዘርን ሲያፋጅ ሲያፈናቅል ኖሯል፡፡

3/ የትግራይ ህዝብ ለዓመታት ከኖረበት ድህነት በማስወጣት ህዝቡን ለልማት ከማዋል ይልቅ ወደ ጦርነት እንዲያመራ ገፋፍቷል፡፡

4/ የሰሜን እዝን በማጥቃት፤ ክልሉን ወደ ጦርነት ቀጠና እንዲያመራ አድርጓል፡፡

እነዚህ እና ሌሎችም ችግሮች እንዳይከሰቱ በክልሉ ወደሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች በተደጋጋሚ ልመናና ሽምግልና ተደርጓል ያሉት ዶ/ር አብይ ፤በግላቸው ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን፤ባለሃብቶችንና የክልሉ ጉዳይ በቅርበት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገራቸውን ነገር ግን ይህ ሳይሆን እንደቀረና ተጠያቂ አመራሮችን በህግ ወደ ሚያስጠይቀው የህግ ማስከበር ዘመቻ መጀመሩን አንስተዋል፡፡

በጦርነት ሂደት ተሳታፊ እና ተጠያቂ አካላትን ብቻ ለመያዝ ጥረቶች መደረጋቸውን ያነሱት ዶ/ር አብይ ክልሉን ካጋጠመው ውድመትና ኪሳራ መልሶ ለማቋቋምና ለማረጋጋትና ህግን ከማስከበር ዘመቻው ጎን ለጎን ክልሉ በጊዜያዊ መንግስት እንዲተዳደር የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውንም አንስተዋል፡፡

በክልሉ በነበረው ጦርነት የተገኘውን ፋይዳን በተመለከተ ሰሜን እዝን ዳግም መመለስ መቻል፤ ከዚህ በኋላ መከላከያ ጠንካራ አቋም ይዞ እንዲገነባ የሚያስችል ልምድ መገኘቱን፤ ኢትዮጲያዊያንን ለመከፋፋል እንዲሁም ለመለያየት ሲሰራ የነበረው ሴራ እምብዛም እንዳይሳካ ከዚህ ጦርነት ልምድ መወሰዱን ያነሱ ሲሆን በትግራይ ዘመቻ ትልቅ ኪሳራን አድርሷል ያሉትም ዘርዝረዋል ጊዜ፤ገንዘብ፤ ከሁሉ በላይ የሰው ሃይል ፤ለ40 ዓመታት የተተከለው የዘረኝነት መርዝ ትልቅ ኪሳራና ጉዳት ሆኖብናል ሲሉ አክለዋል፡፡

በመንግስት በኩል የነበረውን ኦፕሬሽን ግን ባልተገባ መልኩ እንደ ስህተት ሲነገር ነበር ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ግጭቱን ማስቀጠል አሁንም ቢሆን ይቻላል ያሉት ዶ/ር አብይ ነገር ግን ይህንን ማድረግ ኪሳራና ያልተገባ መሆኑን ሊታወቅ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

የፀጥታ ሃይሉ ከትግራይ ክልል እንዲወጣ የተደረገበትን ምክንያት በተመለከተ በክልሉ ያለውን የፀጥታ ሃይል የማስወጣት ዘመቻ አንድ ወራትን ያክል እንደፈጀና በአራት ዙር ይሄንን ትጥቅ የማስወጣት ሂደት መካሄዱን አስታውቀዋል፡፡

ይህንንም በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችን ምላሽና የሚያሳድረውን ውጤት በቅርቡ እናየዋለን ያሉት ዶ/ር አብይ፤ አሁንም ቢሆን ቆም ብሎ ማየት እንደሚበጅና የተወሰነው ውሳኔ ለኢትዮጵያዊያን የሚጠቅምና ውጤት እንደሚያመጣም አስታውቀዋል፡፡

የውልሰው ገዝሙ
ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *