የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አረጋዊ ማሩ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት ከሚፈልገው 4 ሚሊዮን ዜጋ ውስጥ አገልግሎቱን የሚያገኘው 2.73 ሚሊዮን ያህሉ ናቸው ብለውናል፡፡
በአዲስ አበባ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሠጡ 11 እና ከዛ በላይ የመጫን አቅም ያላቸው 16 ሺህ 401 ተሸከርካሪዎች ሲኖሩ ከነዚህ መካከል 2 ሺህ 107 የብዙሀን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡
በተጨማሪም 1 ሺህ 700 ሜትር ታክሲዎች በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ነው የተነገረው፡፡
እንደ አቶ አረጋዊ መንግስት የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞችን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የፐብሊክ ሰርቪስ አቋቁሞ 430 አውቶብሶች አገልግሎት እንዲሰጡ ቢደረግም የትራንስፖርት እጥረቱን ማቃለል አልተቻለውም ብለዋል፡፡
በከተማዋ የትራንስፖርት እጥረት እንዲከሰት በማድረግ የአገልግሎት መስተጓጎል የሚፈጥሩ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ ባለመወሰዱ ችግሩ ተባብሶ እንዲቀጥል አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአገልግሎት መስተጓጎል የሚፈጥሩ አካላት ላይ ቅጣቱን አጠንክረን ለመጣል እየሰራን ነው የሚሉት አቶ አረጋዊ ለአንዱ ባስ 7 ሚሊዮን ብር አውጥተን የገዛናቸው 100 ዘመናዊና ጥራታቸውን የጠበቁ ባሶች ወደ አገልግሎት ሲገቡ የትራንስፖርት ችግሩን በተወሰነ መልኩ ያቃልሉታል ብለን እናምናለን ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የትራንስፖርት እጥረት ችግሩን ለማቃለል የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የሸገር ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶች አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
ሔኖክ ወ/ገብርኤል
ሐምሌ 06 ቀን 2013 ዓ.ም
