ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ ብቻ 70 ሚለዮን ብር ኪሳራ እንደገጠመው አስታወቀ፡፡

ፋብሪካው ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ በነበረው ጊዜ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወደ ምርት ሂደቱ በመግባት በቀን ከ700 እስከ 800 ሺህ መቶ ዳቦ በማምረት በአዲስ አበባ እና ዙሪያ ባሉት ከ400 በላይ ሱቆቹ ምርቱን እያከፋፈለ ይገኛል፡፡

ነገር ግን ፋብሪካው ላለፉት አምስት ወራት በነበረው የምርት ሂደት ለ70 ሚለየን ብር ኪሳራ መዳረጉን አስታውቋል፡፡

ምክንያቱ ደግሞ ፋብሪካው ለስንዴም ሆነ ለምርት ሂደቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ዋጋ ዳቦው ከሚሸጥበት ዋጋ ጋር ሲነፃፀር በፍፁም እንደማይገኛኝ የፋብሪካው የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን እና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ አብድሩሃማን አህመዲን ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው ያሉት አቶ አብዱሮህማን ነገር ግን ይሄን ያክል ሊከስር አይገባም ነበር ብለዋል።

ኪሳራው እንዳይቀጥል እና ፋብሪካው እንዳይዘጋ መንግስት ከስንዴ ጀምሮ ለምርቱ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ማሟላት ይኖርበታል ብለዋል።

ፋብሪካው በአሁኑ ሰዓት በቀን ከ1 ሚለዮን በላይ ዳቦ የማምረት አቅም ቢኖረውም ዳቦውን ወደ ማከፋፈያ ሱቆች ማድረስ የሚያስችል የተሽከርካሪ እጥረት እንደገጠመውም ነግረውናል።

በአሁኑ ሰዓት ሸገር ዳቦ ያመረታቸውን ዳቦዎች ወደ ማከፋፉያ ሱቆቹ ለማድረስ 50 የሚሆኑ ተሸከርካሪዎች ያስፈልጉታል ይሁን እንጂ ፋብሪካው በአሁኑ ሰዓት ያሉት ተሸከርካሪዎች 20 ብቻ በመሆናቸው ችግር ገጥሞናል ብለዋል።

ፋብሪካው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ድጋፍ እንዲያደርግልን ብንጠይቅም መፍትሔ ሊሰጠን አልቻለም ብለውናል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጠን ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም አልተሳካም።

በየውልሰው ገዝሙ
ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *