በኢትዮጵያ ከመቶ እናቶች ውስጥ በወር አበባ ጉዳይ ከሴት ልጆቻው ጋር የሚወያዩት ሁለቱ ብቻ መሆናቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የጤና ሚኒስቴርና ዩኒሴፍ በጋራ ያወጡት ሪፖርት እንደሚሳየው በኢትዮጵያ ከመቶ እናቶች መካከል ከሴት ልጃቸው ጋር በወር አበባ ጉዳይ የሚወያዩት ሁለቱ ብቻ ናቸው ተብሏል።ሴት ልጆቻቸው የወር አበባ ከማየቷ በፊት በጉዳዩ ላይ የሚወያዩት ሁለቱ ብቻ ሲሆኑ ከ10 ሴት ተማሪዎች ደግሞ ከአንድ በላይ የሚሆኑት በወር አበባ ምክንያት ከትምህርት ቤት ይቀራሉ ፡፡

በተጨማሪ ከ3 ሴት ተማሪዎች አንዷ የተጠቀመችበትን የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ወደ ቤት ተመልሳ የምትቀይር ሲሆን ይህም ሊሆን የቻለው ከግማሽ በላይ የሆኑት የትምህርት ቤት መፀዳጃ ቤቶች የውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት እና በወር አበባ ጉዳይ ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ የወር አበባ ንጽህና አጠባበቅ ቀን በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይከበራል፡፡

በሀገራችንም በዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ጌዜም ቢሆን የወር አበባ አይቆምም ጌዜው አሁን ነው በሚል መሪ ቃል ነገ ይከበራል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ቀኑን አስመልክቶ ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ የዘንድሮው በዓል አከባበር ዓላማ ለሴቶችና ልጅ አገረዶች በተለይም ከየአካባቢያቸው ለተፈናቀሉ፣ በመጠለያ ካምኘ ላሉ እንዲሁም በለይቶ ማቆያና ለይቶ ማከሚያ ማዕከላት ለሚገኙት ሴቶችና ልጃገረዶች የሚደረገው የንፅህና መጠበቂያ ድጋፍ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅትም ቀጣይነት እንደሚኖረው ለማሳየት ነው ብሏል፡፡

ከየአካባቢያቸው ለተፈናቀሉ፣በመጠለያ ካምኘና በለይቶ ማቆያ ማዕከላት እንዲሁም በየጤና ተቋማት ላሉ ሴቶችና ልጃገረዶች በሙሉ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ማዳረስ ሌላኛው የበዓሉ አላማ ነው ተብሏል።

እንዲሁም በገጠር አካባቢ ለሚገኙ ልጃገረዶችም በአካባቢያቸውና በቤታቸው ከሚገኙ ቁሳቁስ ንጽህናው የተጠበቀ የወር አበባ መጠበቂያ እንዴት እንደሚሠራ ማስተማር ተገቢ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በወር አበባ ላይ ያለው መገለል እንዲቆምና በዚህ ዓለም አቀፍ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ለተጋላጭ ሴቶችና ልጀገረዶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በማቅረብ የበለጠ ድጋፍ እንደሚያርግም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ።

https://t.me/ethiofm107dot8

በትዕግስት ዘላለም

ግንቦት 19 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *