እንቦጭን ጨምሮ ሌሎች መጤ አረሞች ላደረሱት ጉዳት ብቻውን ሊወቀስ እንደማይገባ የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢኒስቲትዩት አስታወቀ።

ኢኒስቲትዩቱ እንደሚለው ባለፉት 100 ዓመታት ኢትዮጵያ 90 በመቶ የሰብል ዝርያዎቿን አጥታለች።

ሃገር በቀል የሰብል ዝርያዎችን በውጪ ሃገር የሰብል ዝርያዎች በመተካት የበለጠ ምርታማ መሆን ይቻላል በሚል የተሳሳተ አመለካከት ሳቢያም 50 በመቶ የኢትዮጵያ የእንስሳት ዝርያዎችም ሙሉ ለሙሉ ጠፍተዋል።

እነዚህ አገር በቀል የእጸዋት እና እንስሳት ዝርያዎች በመጥፋታቸው ምክንያት ደግሞ አገር በቀል መድሃኒቶችን ማግኘት አለመቻሉን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

አሁን አሁን ደግሞ መጤና ወራሪ የሆኑ ዝርያዎች ለሃገራችን ብዝሃ ህይወት ትልቅ ስጋትን ደቅነዋል፡፡

እስከ 50 ሺህ ሄክታር የሚደርሰውን የጣና ሃይቅን ክፍል እንደወረረው የሚነገርለት እምቦጭ አረም፤አሁን ስጋቱ በመላ ሃገሪቷ ለሚገኙ ታላላቅ ሃይቆችና ወንዞችም ጭምር ሆኗል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያ ብርቅዬ ሃብት የሚባሉ በተለይም በጣና ሃይቅ ላይ ያሉ ብዝሃ ህይወት ሲጠፉ እንዴት ዝም አልክ ስንል የኢትዮጵያ ብዝሃህይወት ኢንስቲትዩትን ጠይቀናል።

የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መለሰ ማሪዮ እንዳሉት እንቦጭን ጨምሮ ሌሎች መጤ አረሞች ባስከተሉት ጉዳት ልወቀስ አይገባም ብሏል።

የሃገሪቷን ብዝሃ ህይወት የመጠበቅ ሃላፊነት የተሰጠን መስሪያ ቤቶች ፤ እስከ ፈረንጆቹ 2020 ድረስ በሃገራችን መጤ ወራሪ ዝርያዎችን ሽፋን 75 በመቶ ለመቀነስ የሚያስችል የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ ተፈራርመን ነበር።

ይሁንና ስምምነት የተፈራረምናቸው የመንግስት ተቋማት አብዛኞቹ ፈርሰዋል ቀሪዎቹ ደግሞ ኬሎች ተቋማት ጋር ተዋህደዋል ይህ መሆኑ ደግሞ እቅዱን እንዳላሳካ እክል ፈጥሮብናል ብለዋል።

ከእምቦጭ አረም በተጨማሪ በሌሎች መጤ ዝርያዎች ምክንያት በርካታ ሄክታር መሬት ከጥቅም ውጪ መሆኑን የነገሩን ዳይሬክተሩ ወደ መፍትሄው መግባት የሚያስችል ልዩ እቅድ እና በጀት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ በሃገራችን ባሁኑ ሰዓት ከመቶ በላይ የሚሆኑ ወራሪ መጤ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡

የጉዳታቸው መጠንም ከግምት በላይ ነው፡፡ እናም ስራው የአንድ ሰሞን ብቻ ሳይሆን ክትትል የሚያስፈልገው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይሁንና ሃላፊነት በተሰጣቸው መስሪያ ቤቶች መካከል ያለው ቅንጅት በጣም ደካማ በመሆኑ የአረሞቹ ጉዳት ሊቀጥል ይችላል ብለዋል፡፡

መስሪያ ቤቶቹ ለኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢኒስቲትዩት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውንና ይህንንም ለፖሊሲ አውጪዎች ማሳወቃቸውን ዶ/ር መለሰ ነግረውናል፡፡

ተቋማቱ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት መወጣት ባለመቻላቸው ችግሩ ሊቀጥል ችሏልም ብለዋል፡፡

በወቅቱ በዚህ የአምስት አመታት የድርጊት መርሃ ግብር ላይ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር፣የግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር፣እንስሳትና አሳ ሃብት ሚኒስትር እንዲሁም የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢኒስቲትዩት ፊርማቸውን ማኖራቸውን ብንመለከትም አብዛኛዎቹ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች እንደገና የተቋቋሙ ወይም ሃላፊዎቻቸው የተቀየሩ በመሆኑ ከ5 ዓመት በፊት ስለተፈረመው ስምምነት መረጃው እንደሌላቸው ነግረውናል፡፡

በነገራችን ላይ በመስሪያ ቤቶች ውስጥ በሚደረግ ሪፎርም ወይም የአመራሮች መቀያየር ውስጥ በርካታ እቅዶች መረሳታቸው በተለያዩ ጊዜያት የምንታዘበው ነው፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በአባይነሽ ሽባባው
ግንቦት 27 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *