ቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ የኮሮና ቫይረስ ስጋት አለመሆኑ ከተረጋገጠበት ጊዜ አንስቶ ከዘጠኝ ወራት እስከ አንድ ዓመት ባሉት ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ ተወሰነ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በሃገሪቱ ስጋት ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ ሁሉም የፌደራልና ክልል ምክር ቤቶች ስራቸውን እንዲቀጥሉ በሚል የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አጽድቋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ እያካሄደ ነው።

የምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምርጫን ከማራዘም ጋር በተያያዘ የቀረበለትን የህገ መንግስት ትርጓሜ ጥያቄ ከአተረጓጎም ፣ መርህ ፣ ዘዴና አላማ ይዘት ጋር ገምግሞ ተገቢውን ምርመራ በማድረግ የውሳኔ ሃሳብ ማሳለፉን አስታውቋል።

1. የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በሃገሪቱ ስጋት ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ ሁሉም የፌደራልና ክልል ምክር ቤቶች ስራቸውን እንዲቀጥሉ ፣

2. ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የጤና ድርጅቶች ኮቪድ19ኝን በተመለከተ የሚያወጡትን መረጃ መሰረት በማድረግ የጤና ሚኒስቴር፣ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የሳይንሱ ማህበረሰብ አካላት ወረርሽኙ የህዝብ ስጋት አለመሆኑን ካረጋገጡና ይህም በምክር ቤቱ ከፀደቀ ሃገራዊ ምርጫውን ከ9 ወር እስከ 1 አመት ማካሄድ እንደሚቻል የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል።

ኮሚቴው ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በማድመጥ እና በውሳኔው ላይ በመወያየት ኮሮና ቫይረስ ስርጭት በሃገሪቱ ስጋት ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ ሁሉም የፌደራልና ክልል ምክር ቤቶች ስራቸውን እንዲቀጥሉ በሚል የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አጽድቆታል።

የውሳኔ ሃሳቡ በአራት ተቃውሞ፣ በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ እና በ114 ድጋፍ በአብላጫ ድምጽ መጽደቁን ምክር ቤቱ አስታውቋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሀም ከትናንት በስቲያ በገዛ ፍቃዳቸው ከሃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

ሆኖም በፌዴሬሽን ምክር ቤት አሰራር ዋና አፈ ጉባኤ ባይኖሩ ምክትሉ ስራውን መምራት ይችላል በሚለው ህግ መሰረት የዛሬው ጉባኤ በምክትል አፈ ጉባኤው እየተመራ ነው፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያዊያን
ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *