የሕዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ሁለተኛ ቀን ውይይት ከሰዓታት በኋላ ይጀመራል

ድርድሩ የደቡብ አፍሪካ፣አውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ታዛቢዎች በተገኙበት እንደሚከሄድ ተገልጿል።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የሙሌት እና ዓመታዊ የውሃ አለቃቅ በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ትናንት ተካሂዷል።

ድርድሩ በበይነ-መረብ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ታዛቢዎች በተገኙበት በውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ተካሂዷል።

በዚህ ድርድር ላይ በደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ በታዛቢነት ተገኝተዋል ተብሏል።

በዚህ ስብሰባ ሀገራቱ የድርድር ስነ-ስርዓትን ታዛቢዎችን፣ ስለ ድርድሩ አካሄድ እና ዋናዋና የድርድር ያልተቋጩ ጉዳዮችን በተመለከተ ተነጋግረዋል።

እያንዳንዱ ሀገር ዋናዋና የድርድር ጉዳዮች ናቸው ያሏቸውን ሃሳቦች በዝርዝር አቅርበዋል።

በዚህም መሰረት በቀጣይ ቀናት ተከታታይ ውይይቶችን ለማድረግ መግባባት ላይ መደረሱ ተገልጿል።

ይሁን እንጂ የታዛቢዎቹ ሚና ምን ይሁን የሚለውን በተመለከተ በሀገራቱ መካከል መግባባት ላይ ያልተደረሰ ሲሆን ስብሰባው በዛሬው ዕለትም የሚቀጥል ይሆናል ተብሏል።

የሶስቱ ሀገራት ድርድር የግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት እና ዓመታዊ አለቃቅ ላይ ብቻ የተወሰነ ሲሆን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ልዩነቶችን በድርድር ለመፍታት ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ዝግጁ መሆኗም ተገልጿል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሙሉቀን አሰፋ
ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *