የደም አይነታቸው O የሆኑ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የመያዝ ዕድላቸው አነስተኛ ነው ተባለ።

የደም አይነታቸው A የሆኑ ሰዎች ደግሞ በኮሮና የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡

በካሊፎርኒያ ግዛት የሚገኘው የአሜሪካ የዘረመል ጥናት ተቋም (US genomics firm) እያከናወነ ባለው ጥናት እስካሁን ከ 750 ሺህ በላይ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን የደም አይነታቸው O የሆኑ ሰዎች ሌላ የደም አይነት ካላቸው ሰዎች ይልቅ በኮሮና የመያዝ ዕድላቸው አነስተኛ እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡

ጥናቱ የደም አይነታቸው O የሆኑ ሰዎች ሌላ የደም አይነት ካላቸው ሰዎች በኮሮና የመያዝና ሆስፒታል የመግባት ዕድላቸው 19 በመቶ ያንሳል ይላል፡፡

እስካሁን የተደረጉ ሌሎች ጥናቶችም ይሄንኑ የሚያረጋግጡ ሲሆን እስካሁን በኮሮና የተያዙ የደም አይነታቸው O የሆኑ ሰዎች ቁጥራቸው አነስተኛ ነው፡፡ የተያዙትም ሌላ የደም አይነት ካላቸው ሰዎች ይልቅ ህመሙ አይፀናባቸውም፡፡

በጥናቱ ከተሳተፉ ሰዎች በኮሮና የተያዙት አብዛኞቹ የደም አይነታቸው AB ነው፡፡
ጥናቱ አሁንም አንደቀጠለ ሲሆን በኮቪድ 19 የተያዙ ፍቃደኛ 10 ሺህ ሰዎች እንደሚፈልግ ተቋሙ ገልጧል፡፡

በመጋቢት በቻይናዋ ውሀን ከተማ የዝሆንግናን ሆስፒታል አጥኚዎች 2 ሺ 173 በኮሮና የያዙ ሰዎች ላይ ባደረጉት ጥናት የደም አይነታቸው A የሆኑ ሰዎች በኮሮና የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው ነበር፡፡

የደም አይነታቸው A የሆኑ ሰዎች ሌላ የደም አይነት ከላቸው ሰዎች ይበልጥ ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸውና ከተጠቁም በኋላ ከሌሎቹ የደም አይነቶች ይበልጥ ከፍተኛ የህክምና ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው ተግልፆ ነበር፡፡

በዚህ ወር መጀመርያ በጣልያንና በስፔን ሳይንቲስቶች 1 ሺህ 980 የኮሮና ተጠቂዎች ላይ የተሰራው ሌላ ጥናት ደግሞ የደም አይነታቸው A ፖዘቲቭ የሆኑ ሰዎች በኮሮና የመጠቃት ዕድላቸው ሰፊ ሲሆን O የደም አይነት ውስጥ ደግሞ በበሽታው የመጠቃት ዕድልን የሚቀንስ ኢለመንት አለው ብለው ነበር፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሔኖክ አስራት
ሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *