ጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር እና የገጠመው የኮሮና ቫይረስ ፈተና

ጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር ባሳለፍነው ረቡዕ 10 ቀን 2012 ዓ.ም የተለመደውን በጎ ተግባሩን በማከናወን ላይ ሳለ ያልጠበቀው ክስተት እንደተፈጠረ አጋርቶናል፡፡

የማህበሩ መስራችና ስራ አስኪያጅ መለሰ አየለ እንደነገሩን በእለቱ አየር ጤና ሀና ማርያም አካባቢ አንድ የአእምሮ ህመምተኛ ከጎዳና አንስተው ከሽሮሜዳ ከፍ ብሎ ቁስቋም 17 ቁጥር ማዞሪያ አካባቢ ወደሚገኘው የማህበሩ ጊቢ ለመውሰድ መንገድ ይጀምራሉ፡፡

ታማሚውንም ወደ ማቆያው ሊያስገቡ የአንቡላንሱን በር በሚከፍቱበት ጊዜ ግን ህመምተኛው ህይወቱ አልፎ ያገኙታል፡፡ በዚህም የተደናገጡት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ እና ባልደረቦቻቸው ጉዳዩን ለፖሊስ ደውለው ያሳውቃሉ፡፡

ፖሊስ በአካባቢው ቢደርስም ከወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከግለሰቡ አስክሬን ናሙና ተወስዶ ውጤቱ እስኪረጋገጥ ድረስ ማንሳት አልተቻለም፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥም ስራ አስኪያጁን ጨምሮ አብረዋቸው የነበሩ አጋዥ ባለደረሰቦቻው ውጤቱ ታውቆ አስክሬን እስኪነሳ ድረስ የትም ሳይሄዱ በዚያው መጠበቅ የግድ እንደሆነባቸው እና አስቸጋሪ ጊዜን እንዳሳለፉ ነግረውናል፡፡

የአስክሬን ናሙናውም በሁለተኛው ቀን ማለትም ሀሙስ ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ የተወሰደ ሲሆን ከኮሮና ቫይረስ ነፃ ሆኖ በመገኘቱ አስክሬኑ እንዲነሳ መደረጉን ነግረውናል፡፡

የማህበሩ ስራ አስኪያጅ እንዳሉን ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ የአእምሮ ህመምተኞችን ከጎዳና ላይ የማንሳቱ ሂደት ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም የገጠሙንን ነገሮች ወደ ጎን በመተው ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ 85 የአእምሮ ህመምተኞን ከጎዳና ማንሳታቸውን ነግረውናል፡፡

በዚህም ወቅት ታማሚዎች ማቆያ ከገቡ በኃላ ልብሳቸውን ለማውለቅ ፣ገላቸውን ለማጠብ እና ቀርቦ እንክብካቤ ለማድረግም በርካታ ፈተናዎች እንደሚገጥሟቸው ነግረውናል፡፡

ከነዚህ መካከል ሰራተኞቻችን ከመፈንከት ጀምሮ አላስጠጋም በሚል ግብግብ ውስጥ የሚገቡ ታማሚዎች በርካቶች መሆናቸውን አጋርተውናል፡፡

ማህበሩ በበጎ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ እና የሰዎችን እርዳታ የሚሻ መሆኑ ወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከሰዎች የሚያገኘውን ድጋፍ አስቀርቶበታል፡፡

ከዚህ ቀደም ድግስ ያላቸው ወደ ማህበሩ መጥተው ታማሚዎችን ይመግቡልን ነበር፣ አልባሳት እንዲሁም የተለያዩ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ያደርጉልን የነበሩ ሰዎችም ቢሆኑ አሁን ላይ ደብዛቸው አእንደጠፋ አቶ መለሰ ነግረውናል፡፡

322 የአእምሮ ህሙማንን ከጎዳና በማነሳት በመርዳት ላይ የሚገኘው ማህበሩ ደጋግ ልቦች ወረርሽኙን ፈርተው ድጋፍ ከማድረግ በመቆጠባቸው አሰቸጋሪ ጊዜን እያሳለፈ እንደሚገኝ ሰምተና፡፡

በመሆኑም ይህንን መልዕክት የምትሰሙ ሁሉ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ለማህበሩ ድጋፍ ማድረግ ከፈላጋችሁ 011 870 39 27 ወይም 0912 18 88 76 ላይ ይደውሉላቸው አልያም ከሽሮሜዳ ከፍ ብሎ ቁስቋም 17 ቁጥር ማዞሪያ አካባቢ ወደሚገኘው የማህበሩ ጊቢ ማቅናትም ትችላላችሁ፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በትግስት ዘላለም
ሰኔ 12 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *