የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ገዥዉ ፓርቲ የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመሸጥ እያደረገዉ ያለዉ ሂደት ግልጸኝነት የጎደለዉና ጥድፊያ የተሞላበት ነዉ ብሏል፡፡
የኢኮኖሚ ዘርፎች ተወዳዳሪነት ዋነኛ ሞተር የሆነን የቴሌኮም ኢንደስትሪ እንደ ተራ መረጃ ማስተላለፍያ ብቻ በማየት ለውጪ ድረጅት ለመሸጥ የጀመረው መንገድ ፍፁም አደገኛ እና የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል ሲል ጠይቋል፡፡
ቴሌኮም ሲሸጥ ገዢዎቹ ከገዙት መጠን በላይ ተፅዕኖ በማሳደር የድርጅቱና የተግባሩ ባለቤቶች ለመሆን ይጥራሉ ያለዉ ፓርቲዉ ይህ በብዙ ሀገራት የታየ ክስተት መሆኑንም ገልጧል፡፡
ከኮቪድ – 19 በኋላ ዓለም ወደምን ዓይነት ኢኮኖሚዊ ሥርዓት እያመራች እንደሆነ መገመት በሚያዳግትበት በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን ማስተላለፍ ከትርፉ ጉዳቱ ያመዝናል።
የሚወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች አሁን ካለንበት ችግር የሚያወጡን ብቻ ሳይሆኑ የወደፊቱንም ትውልድ የምጣኔ ሀብት እና የማኅበራዊ ነፃነቱን በምንም ዓይነት መልኩ አደጋ ላይ የማይጥሉ መሆናቸው መረጋገጥ እንዳለበትም ፓርቲዉ አሳስቧል፡፡
ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የቴለኮም የአከሰዮን ድርሻ ዋጋ ዓለም ላይ በእጅጉ መዉረዱን የሚናገረዉ ኢዜማ፣ በዚህ ወቅት በሚደረግ ፕራይቬታይዜሽን የሚገኝ የውጭ ምንዛሬ መጠን የቱንም ያህል ቢሆን ገዥ ያጣ ንብረት በሚጣልበት ዋጋ እንደተሸጠ ሊታሰብ ይገባል ነዉ ያለዉ፡፡
ሥልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ ያለበቂ ውይይት እና ግልጽነት በጎደለው መልኩ የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ለመሸጥ እሄደበት ያለው ጥድፊያ፣ ከዚህ ቀደም በዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እየተመከሩ የምጣኔ ሀብት ሪፎርም አድርገዉ ሉዓላዊነታቸውን ያጡ ሀገራት ከሄዱበት መንገድ ጋር ተመሣሣይ መሆኑንም አንስቷል፡፡
በመሆኑም በቂ ጥናት ሳይደረግ እና የንብረቱ ባለቤት የሆነው ሕዝብና ወኪሎቹ ሳይመካከሩ በውጭ ጫና እና ማባበያ ላይ ተመስርቶ የወሰነውን ውሳኔ በመቀልበስ የኢቲዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመሸጥ እየሄደበት ያለውን ሩጫ በአስቸኳይ እንዲያቆም ኢ-ዜማ አሳስቧል፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8
በሙሉቀን አሰፋ
ሰኔ 19 ቀን 2012 ዓ.ም
