ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን በቀጣይ በሚያደርጉት ውይይት ላይ ከስምምነት ባይደረስም ግድቡ ውሃ መያዙ እንደሚቀጥል ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በድረገጹ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ በጋራ የመጠቀም እና አብሮ የማደግ መርህን የምትከተል ሀገር ናት፡፡ ይሁንና በራሷ የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም የሌሎችን ፈቃድ ወይም ይሁንታ የማግኘት ግዴታ የለባትም፡፡

በዘንድሮው የክረምት ወቅት ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ ለመያዝ የምትሰራው ስራ 60 በመቶ የሚሆነው የሃገራችን ህዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ የተጀመረውን ጥረት ያግዛል ብሏል፡፡

በአንፃሩ በጋራ ተጠቃሚነት ለማታምነው ግብፅ ‹‹ከእኔ ብቻ ልኑር›› የዘመናት ግትር አስተሳሰቧ እንድትወጣና በፍትሃዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት ምህዋር ላይ እንድትሽከረከር ያደርጋታል፡፡

ግብፅ በቀጠናውም ሆነ በአህጉሪቱ ላይ ሁለንተናዊ ብልጫን መያዝ ስለምትፈልግ ግድቡ ውሃ እንዳይያዝ ዓለም አቀፍ ተቋማትን በመጠቀም ተፅዕኖ ለማሳደር ስትሞክር ትታያለች፡፡

ይህም ድርጊቷ የሃገራችንን ውሳኔ የሚቀለብስ ባይሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ በሃገራቱ መካከል ፍጥጫ እየተካረረ እንዲመጣ አድርጓል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኃላፊነቱን ወስዶ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ መሪዎችን በመጋበዝ ዓርብ ምሽት ሰኔ 19 ቀን 2012 ዓ.ም ውይይት ማድረጋቸው በዚህ መነሻነት ነው።

ውይይቱ የሃገራትን የተናጠል ፍላጎት ወደ ፍትሐዊና የጋራ ተጠቃሚነት ለማምጣት ያለመ ሲሆን የግብፅ ሚዲያዎች ግን ከውይይቱ መንፈስ ውጪ ‹‹ኢትዮጵያ ስምምነት ላይ ሳይደረስ የውሃ ሙሌቱን ላለመጀመር ተስማማች›› የሚል የተሳሳተ ወሬ በመንዛት ላይ ይገኛሉ። ይህንንም የአፍሪካ ህብረት ተችቶታል፡፡

እውነታው ግን እነሱ እንደሚሉት ሳይሆን ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ የምታከናውነውን ቀሪ ስራና የራሷን ጥቅምና ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ እንጂ በፍራቻና በተፅዕኖ የሚራዘምም የውሃ ሙሊት የማይኖር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ብሏል ተቋሙ በመግለጫው፡፡

ሁሉም ሰው እንደሚያውቀው በዘንድሮው ክረምት ውሃ እንይዛለን ተባለ እንጂ በየትኛው ቀን ላይ ውሃ የመያዝ ስራው እንደሚጀምር ቀድሞውንም ይፋ አልተደረገም።

ሐምሌ የሚለው ወር የተመረጠው ክረምቱ የሚገባበት ወር በመሆኑ ሐምሌ 1 የመሙላት ሂደቱ ይጀመራል ተብሎ አልተነገረም፡፡

ስለሆነም እስከቀሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ድረስ ኢትዮጵያ ግድቡን በውኃ ላለመሙላት የተስማማችበትን ምክንያት አንሻፎ ማቅረብ ህዝባችን በግድቡ ላይ የያዘውን ወጥ አቋም በመሸርሸር ህዝባዊ ድጋፉን ለማሳጣት ከማለም ውጭ ሌላ የተለየ ትርጉም አይሰጠውም፡፡

በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት የሚለው ቃል የተመረጠው በዘፈቀደ ሳይሆን ውሃ ለመያዝ ወሳኝ የሚባሉ የግድቡ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅና በዚህ ዓመት 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ሜ.ኪ. ውሃ የሚተኛበትን መሬት በማፅዳት የደን ምንጣሮ ሥራውን በፍጥነት ለመከናወን ሲባል ነው፡፡

ይህ ውሳኔ እንደሀገር ውሃውን ለመያዝ አሁንም ጽኑ አቋም እንዳለን የሚያሳይ እንጂ የግብፅ ሚዲያዎች እንደሚሉት የኢትዮጵያን ተሸናፊነትና የግብጽን አሸናፊነት አያሳይም፡፡

ድርድሩን ከግድቡ ውሃ መሙላት ጋር ማያያዝ ተገቢ እንዳልሆነ ከሚያሳዩን ጉዳዮች አንዱ ሦስቱ ሀገራት እ.ኤ.አ. በ2015 ማርች ላይ የተስማሙበት የመርሆዎች ስምምነት ኢትዮጵያን የግድቡን ግንባታ እያከናወነች ውሃ ለመያዝ የሚከለክላት አለመሆኑ ነው፡፡

የግድብ ግንባታው ደግሞ ኮንክሪት ሞልቶ መተው ሳይሆን ውሃ ይዞ ኤሌክትሪክ ማመንጨት ስለሆነ ኢትዮጵያ በዚሁ ስሜት እተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡

በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የተጀመረው ውይይትም አጀንዳውን ዓለም ባንክና ከአሜሪካ እጅ አውጥቶ አፍሪካዊ በማድረግ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ለማምጣት የታሰበውን የህብረቱን ዓላማ የሚደግፍ ነው፡፡

ኢትዮጵያም በአፍሪካ ወንድሞቿ ፊት በተፈጥሮ ሀብቷ ለመበልፀግ የምታደርገው በፍትሐዊ ተጠቃሚነትና በጋራ የመልማት ፍላጎትን ላይ የተመሰረተ መሆኑን ለማሳየት ከፍተኛ ዕድል ይሰጣታል ሲል ተቋሙ መግለጫውን ቋጭቷል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያዊያን
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *