የአፍሪካ ኅብረት በህዳሴ ግድቡ የድርድር ውጤት ሪፖርት ላይ ነገ እንደሚመክር ይጠበቃል።

የአፍሪካ ኅብረት ጠቅላላ ጉባዔ ቢሮ በህዳሴ ግድቡ ድርድር ዙሪያ ሦስቱ ተደራዳሪ ወገኖች ስምምነት በደረሱባቸውና ባልተግባቡባቸው ጉዳዮች ላይ መክሮ ውሳኔውን ለማሳወቅ ነገ እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል።

ይህ ስብሰባ በአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ እንደሚመራ የአፍሪካ ሕብረት በድረገጹ አስታውቋል።

በዚህ ስብሰባ ባሳለፍነው ሳምንት ያለ ስምምነት የተጠናቀቀው የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደር ድርድር አጠቃላይ ሪፖርትን እንደሚገመግም ተገልጿል።

የአፍሪካ ኅብረት ጠቅላላ ጉባዔ ቢሮ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ባካሄደው ስብሰባ ታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ግብፅና ሱዳን መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የአደራዳሪነት ሚናውን የአፍሪካ ኅብረት እንዲይዝ በወሰነው መሠረት፣ ሦስቱ አገሮች ለ11 ቀናት ሲደራደሩ መቆየታቸው ይታወሳል።

በዚህ ድርድር ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም መሠረታዊ በሚባሉ ጥቂት ነጥቦች ላይ መቀራረብ ባለመቻላቸው ድርድሩ መቋረጡ አይዘነጋም።

በዚህም ምክንያት የድርድሩን አጠቃላይ ይዘትና የልዩነት ጭብጦችን ከእነ ምክንያቶቻቸውና የመፍትሔ ሐሳቦቻቸው፣ ሦስቱም አገሮች በተናጠል ለኅብረቱ ሪፖርት አቅርበዋል።

የአፍሪካ ኅብረትን በመወከል ድርድሩን የመሩት የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ተወካይና የኅብረቱ የባለሙያዎች ቡድን የጋራ ሪፖርትም፣ ለኅብረቱ ቀርበዋል።

የኅብረቱ ጠቅላላ ጉባዔም በነገው ስብሰባ የቀረቡትን ሪፖርቶች ገምግሞ፣ በቀጣይ አቅጣጫ ላይ ከሦስቱ አገሮች መሪዎች ጋር እንደሚወያይ ይጠበቃል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በአባቱ መረቀ
ሐምሌ 13 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *