ታላቁ የህዳሴው ግድብ ውሀ መያዙን ተከትሎ “አባይ ተገርቶ ወንዝም ሐይቅም ሆነ” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።

ታላቁ የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ዓመት የዉሃ ሙሌቱ ተጠናቋል ተብሏል።

ግድቡ ውሃ መያዙን ተከትሎ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በትዊተር ገጻቸው እንዳሰፈሩት “አባይ ወንዝ ነበር ተገርቶ ወንዝም ሀይቅም ሆነ” ብለዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም ግድቡ ውሃ ከያዘባት ቅጽበት አንስቶ “አባይ በወንዝነቱ ይፈሳል፣ በሐይቅነቱ ኢትዮጵያ ለፈለገችው ልማት ሁሉ ለመዋል እጅ ሰጥቷል፣ አባይ የእኛ ሆነ” ሲሉም ታሪካዊ ሃሳባቸውን አስፍረዋል።

የአፍሪካ ህብረት አባላት ቢሮ መሪዎች በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በትናንትናው እለት መወያየታቸው ይታወሳል።

በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበርና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ መሪነት በቪዲዮ ኮንፈረንስ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ተሳትፈዋል።

በዉይይቱ በአበይት ጉዳዮች ላይ ስምምነት መደረሱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ከውይይቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በነበረው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የግድቡ የመጀመሪያ ዓመት የዉሃ ሙሌት መጠናቀቁም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

ሙሌቱ ተጠናቅቆ የወንዙ ዉሃ በግድቡ አናት ላይ መፍሰስ መጀመሩን ኢትዮጵያ በድርድሩ ወቀት አስታውቃለች።

ከቀናት በፊት የዉሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ በሰጡት መግለጫ በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ግድቡ ዉሃ መያዝ መጀመሩን ገልጸው የመጀመሪያው ዓመት የዉሃ ሙሌት ተሳክቶ ዉሀው በግድቡ አናት ላይ መፍሰስ ይጀምራል ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያውያን
ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *