በኢትዮጵያ በ COVID-19 ተጽዕኖዎች ተጎጂ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የ200 ሚሊየን ብር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

የህብረተሰብ የተፋጠነ የንፁህ ውሃ አቅርቦት ፣ የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና ፕሮጀክት (COWASH) በኢትዮጵያ በ COVID-19 ተጽዕኖ ተጎጂ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ምላሽ ለመስጠት ለ 6 ወራት የሚቆይ የ200 ሚሊየን ብር ፕሮጀክት ዛሬ በአዲስ አበባ በይፋ አስጀምሯል።

ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያና በፊንላንድ መንግስት መካከል የሚተገበር የሁለትዮሽ የትብብር መረሀ ግብር ሲሆን በውኃ ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ስር የተቋቋመ ነው፡፡

በፕሮጀክቱ መክፈቻ ወቅት ንግግር ያደረጉት የውሃ ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ነጋሽ ዋግሾ እንዳሉት ኘሮጀክቱ የህብረተሰቡንና የመንግሥትን አቅም በመጠቀም አዳዲስ የውሃ አቅርቦት ፋይናንስ በማድረግ የውሀ መሠረተ ልማት አቅርቦትን ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

የ COWASH ዋና የቢሮ ሀላፊ ሚስተር አርቶ ሱአሚነን በመድረኩ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ በ COVID-19 ተጽዕኖዎች ተጎጂ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠት አንስቶ መልሶ ማቋቋምን ጭምር ታላሚ ያደረገ የኤክስቴንሽን ፕሮጄክት ነው ብለዋል።

መረሀ-ግብሩ በፊንላንድ መንግሥትና በኢትዮጵያ መንግሥት የገንዘብ መዋጮ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ለ6 ወር የሚቆይ ብሮጀክት ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት 81.4 ሚሊዮን ብር ለስራው የሚውል የጀት መዋጮ ፈሰስ ያደረገ ሲሆን የፊላንድ መንግስት በአንፃሩ 2.6 ሚሊየን ዩሮ ወጪ በማድረግ ፕሮጀክቱን ይደግፋል፡፡

ፕሮጀክቱ በጠቅላላ 200 ሚሊየን ብር የተመደበለት መሆኑም ታውቋል።

የውሃ ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት ልማት ኮሚሽነር ዶ/ር ባሻ ሞገስ በበኩላቸው COWASH ላለፈት 9 አመታት በኢትዮጵያ በ76 ወረዳዎች የመንገድ ንፁ ውሀ ፤ በአካባቢ ፅዳትና በግል ንፅህና አጠባበቅ ዙሪያ በርካታ ስራዎች ሲተገብር መቆየቱን አንስተዋል።

ፕሮጀክቱ ማህበረሰብ አሳታፊ መሆኑ በኢትዮጵያ ትልቅ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረው ከኮቪድ-19 መከላከል ጋር በተገናኘ ለ6 ወራት በሚቆየው ኘሮጀክትም በህብረተሰቡ ዘንድ መልካም ውጤት እንደሚያስገኝ እምነት አለኝ ነው ያሉት

COWASH እንደ አውሮፓውያኑ ከሰኔ 2011 እስከ ታህሳስ 2020 ድረስ በተፋጠነ የህብረተሰብ ንፁህ ውሃ አቅርቦት ፣ በአካባቢ ንፅህናና በግል ንፅህና አጠባበቅ ላይ ሲሰራ የቆየ ፕሮጄክት ነው።

COWASH በኢትዮጵያ ዋን ወሽ የተሰኙ አለም አቀፍ ፕሮግራሞችን ጨምሮ በርካታ ስራዎችን በአማራ ፤ በትግራይ ፤ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ፤ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ይሰራል።

በደረሰ አማረ
ሐምሌ 21 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *