ኢትዮጵያ በቀጣዩ በጀት ዓመት 18 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት የጨረታ ሰነድ በማዘጋጀት ላይ መሆኗ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም አጠቃላይ ስራዎችን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

እንደ ስራ አስፈጻሚው ገለጻ ኢትዮጵያ ለ2013/14 የምርት ዘመን 18 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት የጨረታ ሰነድ እየተዘጋጀ ነው።

ኢትዮጵያ በ2012/13 የበልግ እና የመኸር ግብርና ስራዎች 17 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከህንድ ፣ሞሮኮ፣ቻይና፣ግብጽ እና ከተባበሩት አረብ ሂሚሬቶች መግዛቷ ተገልጿል።

ይህንን የአፈር ማዳበሪያም የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት እንዲያጓጉዝ ቢመረጥም በአቅም ማነስ ምክንያት በጀርመኖቹ ዲኤችኤል እና ዳይመንድ ቡከር ኩባንያዎች መጓጓዙ ተገልጸፇል።

አሁን ላይ በአገር ውስጥ ለቀጣዩ የመኸር ግብርና ስራ የሚውል በቂ የማዳበሪያ ምርት ክምችት መኖሩንም ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

በ2013/14 የበልግ እና የመኸር ግብርና ስራዎች 18 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ስራ አስፈጻሚው የግብርና ሚኒስቴር የግዥ ጨረታ ሰነዱን እያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰነዱ ዝግጅት እንደተጠናቀቀ ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት ማዳበሪያውን ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ይደረጋልም ብለዋል።

ስራ አስፈጻሚው አክለውም በአፈር ማዳበሪያ ግዥና አቅርቦት ወቅት የነበረውን የደላሎች ጣልቃ ገብነት በማስቆም 3 ነጥብ 4 ቢሊዬን ብር ማዳኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎትን በአገር ውስጥ ለማምረት ወደ ስራ ከገባች ከ10 ዓመት በላይ ቢሆናትም እስካሁን የአፈር ማዳበሪያ ሙሉ ለሙሉ ከውጭ አገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በመግዛት ላይ ትገኛለች።

በሙሉቀን አሰፋ
ሐምሌ 22 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *