በኢትዮጵያ በኮሌራ ምክንያት የ8 ሰዎች ህይወት ማለፉን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ እስከ ሀምሌ ወር የመጨረሻው ሳምንት 145 ሰዎች በኮሌራ ወረርሽኝ ሲያዙ 8 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሌራ በሽታን በተመለከተ የሕብረተሰብ ጤና ስጋቶች እና ምላሽ አሰጣጥ ላይ ለጣቢያችን በላከው መግለጫ በአገር አቀፍ ደረጃ እስከ ሃምሌ የመጨረሻው ሳምንት በተለያዩ አካባቢዎች የኮሌራ በሽታ ተከስቶ እስካሁን 145 የሚሆኑ ሰዎች አዲስ በበሽታው ሲያዙ 8 ሰዎች ደግሞ በኮሌራ ምክንያት ህይወታቸውማለፉን አስታውቋል፡፡

በደቡብ ክልል በ6 ወረዳዎች እና በኦሮሚያ ክልል በ1 ወረዳ የኮሌራ ወረርሽኝ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ይህ አሃዝ ከባለፈው ሳምንት ሪፖርት ጋር ሲነጻጸር በ50 በመቶ መቀነሱ ታውቋል፡፡

እስከ ሃምሌ የመጨረሻው ሳምንት ድረስ በምዕራብ ኦሞ ዞን ፣ በጋጪት እና በጎርጎርሻ ወረዳዎች በአዲስ መልክ በሽታው መከሰቱም ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡

የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል የህክምና አገልግሎት የማስፋፋት፣ የውሃ ንጽህና መጠበቂያ ኬሚካሎችን የማሰራጨት፣ የቤት ለቤት ርጭት እና በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች የማፈላለግ እና የክትትል ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋልም ተብሏል፡፡

በተጨማሪም እስከ ሃምሌ ወር የመጨረሻ ሳምንት ድረስ በሃገር አቀፍ ደረጃ ለወባ በሽታ ከተመረመሩት ውስጥ 27 ሺ 898 ሰዎች ምልክት የታየባቸው ሲሆን 2 ሰዎች በዚሁ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል፡፡

በሃገራችን በ42 ወረዳዎች ና በ19 ዞኖች የወባ ወረርሺኝ ተከስቷል፤ በኦሮሚያ 7 ዞኖችና 15 ወረዳዎች ፣ በደቡብ 1 ዞንና በ2 ወረዳዎች ፣ በአማራ በ 7 ዞኖችና በ21 ወረዳዎች ፣ በሶማሊያ በ1 ዞንና በ1 ወረዳ እንዲሁም በትግራይ በ3 ዞኖችና በ3 ወረዳዎች ወረርሺኙ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ሲሆኑ የምላሽ ስራ እየተሰራባቸው ነው ተብሏል፡፡

በተመሳሳይም እስከ ሃምሌ ወር መጨረሻ ድረስ በሃገራችን 32 ሰዎች ፖሊዮ እንደተገኘባቸው ተነግሯል፡፡

በዚህ ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሐረርጌ በቦኬ ወረዳ እና በአዳማ ከተማ 2 ሰዎች በፖሊዮ መያዛቸውን ከኢንስቲትዩቱ ሪፖርት ተመልክተናል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በትግስት ዘላለም
ነሀሴ 13 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *