አዋሽ ቁጥር 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ በጎርፍ እና በእንቦጭ አረም ምክንያት ሀይል ማመንጨት አቆመ።

በአዋሽ III የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ የጎርፍ መጥለቅለቅ በማጋጠሙ ከቅዳሜ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ጣቢያው ለጊዜው አገልግሎት ማቋረጡን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአዋሽ II እና III ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲሳሳ ገልሜሳ አስታውቀዋል፡፡

አቶ ዲሳሳ እንዳስታወቁት በአዋሽ ወንዝ ላይ እየተከሰተ ያለው ጎርፍ እና የእንቦጭ አረም በቆቃ፣ በአዋሽ II እና III የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የወደፊት ዕጣ ፋንታ ላይ ትልቅ ሥጋት ሆኗል፡፡

በአዋሽ ተፋሰስ ላይ የተገነቡት ሶስቱ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በድምሩ 107 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዲኖራቸው ተደርገው የተገነቡ ሲሆን የተፈለገውን ዓመታዊ የኃይል ምርት ለማግኘትም የጎርፍ አደጋ እና የእንቦጭ አረም ዘላቂ መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

በአዋሽ ወንዝ ሙላት የተነሳ ከቆቃ ግድብ ከሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሰከንድ 60 ሜትር ኪዩብ ውኃ ሲለቀቅ ቆይቷል፡፡

ይሁንና ወደ ግድቡ የሚገባው የውሃ መጠን በየጊዜው እየጨመረ በመሆኑ ከግድቡ የሚለቀቀው የውሃ መጠን አሁን ላይ በሰከንድ 625 ሜትር ኪዩብ ውሃ መድረሱን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ላለፉት 49 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውና 32 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የአዋሽ III የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በውሃ መጥለቅለቅ አደጋ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ አገልግሎት መስጠት አቁሟል፡፡

ከተርባይን ወለል እስከ ተርባይን ሮተር ማገናኛ ዘንግ (Turbine Rotor Coupling Shaft) ድረስ ያሉት የኤሌክትሮ-መካኒካል እቃዎች በውሃ በመዋጣቸው የጉዳቱን መጠን ለማወቅ እንዳልተቻለ አቶ ዲሳሳ ተናግረዋል፡፡

የአዋሽ II የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ደግሞ የውሃ መቀበያ (water intake) በእንቦጭ አረም በመዘጋቱ ከሀምሌ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎቱ የተቋረጠ ሲሆን ችግሩን በጊዚያዊነት ለመፍታት አረሙን በኤክስካቫተር የማንሳት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ ዲሳሳ ገለፃ በአዋሽ ተፋሰስ ላይ የሚገኙ የቆቃ፣የአዋሽ II እና III የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የሚገጥማቸውን ተፈጥሯዊ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የቅንጅት ሥራ ያስፈልጋል ማለታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ያደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን እና የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በጋራ በመሆን ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት እንዳለባቸው አቶ ዲሳሳ ጠቁመዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያን
ነሀሴ 26 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *