በመተከል ዞን ከታጣቂ ሀይሎች ጥቃት እራሳቸውን ለመጠበቅ በሚል በጫካ ውስጥ ተሸሽገው የነበሩ ከ300 በላይ ዜጎች ወደ ቄያቸው ተመለሱ፡፡

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ በታጣቂ ሀይሎች ከተሰነዘረው ጥቃት ሸሽተው በጫካ ውስጥ ተደብቀው የነበሩ 12 የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ 310 በላይ ንፁሀን ዜጎች በፌደራልና በክልል የፀጥታ ሀይሎች በተሰራ ኦፕሬሽን ወደ ቄያቸው መመለሳቸው ተገለፀ፡፡

በቅርቡ ጳጉሜ 2 ቀን 2012 ዓ.ም በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ኤርታል ቀበሌ ላይ በታጣቂ ሀይሎች በተሰነዘረ ጥቃት የአካባቢው ሰላማዊ ሰዎችን እና በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች ወደ ጫካ ተበታትነው እንደነበረ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ጃራ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽነሩ እንዳሉት 12 የጤና ባለሙያዎች እና የልማት ጣቢያ ሰራተኞች በወቅቱ ከተፈጠረው ጥቃት በመሸሽ በጫካ ውስጥ እራሳቸውን ደብቀው መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡

ሆኖም በፌደራልና በክልል የፀጥታ ሀይሎች በተሰራ ኦፕሬሽን በህይወት ተገኝተው ወደ ቀበሌያቸው እንዲመለሱና ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲመሩ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር 300 የሚሆን ንፁሀን የማህበረሰብ ክፍሎች በተመሳሳይ ከጥቃቱ ሸሽተው በቀበሌው በቅርብ እርቀት ወደሚገኝ ጫካ እራሳቸውን የሸሸጉ መሆኑን ገልፀዋል ም/ል ኮሚሽነር ነጋ

እነዚህንም ዜጎች ወደ ቄያቸው መመለስ መቻላቸውን እና ሰላማዊ ህይወታቸውን እንዲመሩ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

ታጣቂዎቹን የመደምሰስ ስራው በመካሄድ ላይ ነው ያሉት ኮሚሽነር ነጋ በጫካ እራሳቸውን የደበቁ ንፁሀን ዜጎችን ወደ ቄያቸው የመመለስ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል በማለት ነግረውናል፡፡

ሙሉ በሙሉ የኦፕሬሽን ስራው እንደተጠናቀቀ በተደራጀ መልኩ ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡

በመተከል ዞን ወንበራ ወረዳ የተፈጠረውን ተመሳሳይ ጥቃት ለመቀልበስ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ሀይሎች ገብተው የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስራ ተጀምሯል ብለዋል፡፡

ሙሉ የኦፕሬሽን ስራው እንደተጠናቀቀ መረጃው ለህዝብ ይፋ ይሆናል ብለዋል፡፡

በመተከል ዞን ቡለን እና ወንበራ ወረዳ ላይ የፀጥታ ችግር ከመከሰቱ በፊት በጉባ ወረዳም እነዚህ የታጠቁ ሀይሎች ገብተው በንፁሀን ዜጎች ላይ ጥቃት መሰንዘር የጀምረው እንደነበር ይታወቃል፡፡

በደረሰ አማረ
መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *