የውጭ አገራት ጉዞ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ውጤት ማፍጠኛ በሚል እስከ 600 ብር ሙስና እየተጠየቁ መሆኑን ተናገሩ።

በርካታ አገራት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ጥለውት የነበረውን የጉዞ እገዳ በማንሳት ላይ ናቸው።

አገራቱ የጉዞ እገዳቸውን ሲያነሱ መንገደኞች ከኮሮና ቫይረስ ነጻ መሆናቸውን የምርመራ ውጤት ይዘው እንዲመጡ በቅድመ ሁኔታነት አስቀምጠዋል።

በዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያዊያን ወደ ተለያዩ አገራት ጉዞ ለማድረግ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላብራቶርስ ምርመራ ያደርጋሉ።

ይሁንና የምርመራ ውጤታቸውን ሄደው ለመቀበል ሲሞክሩ መንገላታት እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል።

መንገደኞቹ እንዳሉት የምርመራ ውጤቱን ለመቀበል ስንሞክር ያጉላሉናል፣ውጤታችሁ አልደረሰም በማለት ውጤቱ እንዲፈጥን 600 ብር ክፈሉ ይሉናል ብለውናል።

ብሩን ካልከፈልን ግን ያንገላቱናል ውጤቱንስንጠብቅ ለምግብ እና ለሆቴል ተጨማሪ ወጪ እንድናወጣ በረራም እያመለጠን ነው መንግስት አሰራሩን ሊያስተካክል ይገባል ሲሉ ቅሬታቸውን ነግረውናል።

በኢትዮጵያ ክሊኒካል ላብራቶርስ የቢዝነስ ልማት ዳይሬክተር ሲስተር አጸደ ከሀሊ በበኩላቸው ለመንገደኞች የምርመራ ውጤት ከ48 ሰዓት እስከ 60 ሰዓታት ውስጥ ነው የምናደርሰው ብለዋል።

በመሆኑም እኛ ውጤት አናዘገይም ነገር ግን ያልተገባ ጥቅም ወይም ክፍያ የሚጠይቁ ሰራተኞች ሲያጋጥሙ በቀጥታ ለእኛ ቅሬታ ያቅርቡልን እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ ነግረውናል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም የመንገደኞቹን ቅሬታ ይዞ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትንም ጠይቋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ በበኩላቸው በግል የጤና ተቋማት ላይ የቀረበውን ቅሬታ እውነት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አገልግሎት በሚሰጥበት ጊዜ የሚፈጠሩት ክፍተቶች እና እንግልቶች የመጡትም ምርመራው የሚሰጡት ተቋማቶች ውስን በመሆናቸው ነው ብለውናል፡፡

እንደ ኮሮና ቫይረስ ያሉ ወረሽኞችን ለመከላከል በመንግስት አቅም ብቻ የሚሸፈን አይደለም በመሆኑም የግል ተቋማቶች ተሳትፎ ያስፈልጋል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሔኖክ ወ/ገብርኤል
መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *