የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመንገደኞች የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ የመድን ሽፋን እንደሚሰጥ አስታወቀ።

በአፍሪካ አቪዬሽን ኢንደስትሪ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥቅምት 01 ቀን 2020 እስከ መጋቢት 31 ድረስ የሚቆይ የኮቪድ_19 መድህን ሽፋን ለመንገደኞቹ እንደሚሰጥ ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የመድህን ሽፋኑ መንገደኞች እንደየሚሰማቸው ህመም ወደ ሀገርራቸው መመለስን ጨምሮ የኳራንታይን እና የኮቪድ-19 ህክምና ወጪን ያካትታል ተብሏል።

ተሳፋሪዎች በጉዟቸው ወቅት በኮቪድ-19 ከተያዙ እስከ 100 ሺህ ዩሮ የሚደርስ የህክምና ወጪያቸውን አየር መንገዱ ይሸፍናል፡፡ እንዲሁም በቀን እስከ 150 ዩሮ ቢበዛ የ14 ቀን የኳራንታይን ወጪያቸውን የሚሸፍን መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም እንዳሉት ሼባ ኮንፈርት የሚል ስያሜ የተሰጠው ዓለም አቀፍ የመድህን ሽፋኑ የመንገደኞችን የጤና ደህንነት ለመጠበቅ እንዲሁም ሙሉ ደህንነት እንዲሰማቸው አየር መንገዱ ከወሰዳቸው የደህንነት እርምጃዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡

አክለውም የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ መድህን ሽፋን በመስጠት ከዓለም አቀፍ አየር መንገዶች መካከል በመመደባችን ደስ ብሎናል በማለት ተናግረዋል፡፡ .

የመድህን ሽፋኑ በሁሉም የአየር መንገዱ ዓለም አቀፍ በረራዎች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።

በደረሰ አማረ
መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *