በመንግስት የተዘነጉት ተመራቂ የሕግ ተማሪዎች

ቀደም ሲል ሀገር አቀፉ የህግ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ከህዳር 1-4 ድረስ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰጥ አቅጣጫ ተቀምጦ የነበረ ቢሆንም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር በአንፃሩ ከጥቅምት 23 እስከ 30 ድረስ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለተመራቂ ተማሪዎች ጥሪ እንዲያደርጉ ወስኗል።

ለኢትዮ ኤፍ ኤም ቅሬታቸውን ያቀረቡ የ5ተኛ ዓመት የህግ ተማሪዎች ፈተናውን የምንወስድበት ቀንና ወደ ግቢ እንድንገባ የተቆረጠው ቀን ምንም አይነት የዝግጅት ጊዜ የማይሰጥ ከመሆኑም በላይ በተጣደፈ ሁኔታ እንድንፈተን እየተገደድን ነው በማለት ተናግረዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ5ተኛ ዓመት የህግ ተማሪ የሆነው ፀጋ አየለ ለጣቢያችን እንደገለፀው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ፈተናውን እንደምንወስድ መርሀ ግብር የወጣ ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ሊቋረጥ ችሏል፡፡

አሁን በወጣው መረሀ ግብር መሰረት ከጥቅምት 23 እስከ 30 ድረስ ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው እንዲገቡ አቅጣጫ ተቀምቷል፡፡

በሌላ መልኩ ሀገር አቀፍ የህግ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና የሚሰጥበት ቀነ-ገደብ ከህዳር 1 እስከ 4 ነው፡፡

የወጣው ፕሮግራም ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደገባን ፈተና ላይ እንድንቀመጥ የሚያስገድደን ነው፡፡ በቂ የዝግጅት ጊዜ አልተሰጠንም፡፡

ሆኖም በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ጥቅምት 30 ወደ ግቢ የሚገባ ተማሪ በነጋታው ፈተና ላይ እንዲቀመጥ ይገደዳል፡፡

በብዙ ምክንያቶች 1 ቀን ዘግይቶ የሚገባ ተማሪማ ጭራሽ ፈተናው ላይ አይደርስም ይላል ተማሪ ፀጋ አየለ፡፡

ከ15 ቀናት በፊት ቀድመን መግባት ሲኖርብን አልያም ወደ ግቢ ከገባን በኋላ ቢያንስ የ15 ቀናት የመዘጋጃ ጊዜ በተሰጠን ነበር፡፡ ያ ባለመሆኑ በተጣደፈ ሁኔታ ሀገር አቀፍ ፈተናውን እንድንወስድ እየተደረግን ነው ሲል ነግሮናል፡፡

ሌላኛዋ ኢትዮ ኤፍ ኤም ያነጋገራት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የ5 ዓመት የህግ ተማሪ ዮርዳኖስ ግርማ በበኩሏ በኮቪድ ምክንያት ከዩኒቨርሲቲ እንድንወጣ ሲደረግ ለፈተናው የምናነባቸውን በቂ ሀንዳውቶችና ሞጁሎችን ይዘን አልወጣንም፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ከወጣን በኋላም ወደ ስራ በመሰማራታችን በቂ የማንበቢያ ጊዜ አልነበረንም፡፡ በመሆኑም ወደ ግቢ የምንገባበትና ለመውጫ ፈተናው የምንቀመጥበት ጊዜ ሰሌዳ የተጠጋጋ በመሆኑ ዳግም ሊጤን ይገባል ትላለች፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤምም የተማሪዎቹን ቅሬታ ፈተናውን ለእጩ ተመራቂዎች የሚያዘጋጀው ለፌደራል ፍትህ እና ህግ ምርምር ኢኒስትቲዩት አቅርቧል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የህግ ትምህርትና ስልጠና ማሻሻያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ መስፍን እሸቱ ለጣቢያው በሰጡት ምላሽ ፈተናውን ያለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ለመስጠት ተወስኖ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን በኮቪድ ምክንያት ማከናወን አለመቻሉን ገልፀው ለዘንድሮ መተላለፉን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ሀገር አቀፍ የህግ ትምህርት ቤቶቹን የሚወክሉ አካላት ማለትም የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ፤ አገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ ፤ ለፌደራል ፍትህ እና ህግ ምርምር ኢኒስትቲዩት ፤ የህግ ትምህርት ቤቶች ማህበር እና ተወካዮች በተገኙበት ከህዳር 1 እስከ 4 ለመስጠት ተወስኗል፡፡

በዚህም ኢንስቲትዩቱ ለሁሉም ዩኒቨርስቲዎች በተወሰነው ቀን ፈተናው እንዲሰጥ ደብዳቤ መላኩን አመልክተዋል፡፡ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ጋር የነበረን ስምምነት የህግ ተማሪዎች ለፈተናው ሲባል ከሌሎች ተማሪዎች ቀደም ብለው ይገባሉ የሚል ነበር ይላሉ፡፡

ይሁን እንጂ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ከ45ቱም የዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንቶች ጋር ባካሄደው ስብሰባ አጠቃላይ ተመራቂ ተማሪዎች ከጥቅምት 23 እስከ 30 እንዲገቡ ወስኗል፡፡ በዚህም ሳቢያ የፕሮግራም መጠጋጋት ሊፈጠር ችሏል ይላሉ፡፡

ሆኖም ይህንን የፕሮግራም መጠጋጋት በተመለከተ በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው አጠቃላይ የህግ ትምህርት ቤቶች ስብሰባ ላይ እንደገና ለማጤን ይሞከራል፡፡ በስብሰባው ጉዳዩን የተመለከተ አንድ ውሳኔ ላይ ይደረሳል ብለን እንጠብቃለን ፤ እርሱን ውሳኔ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር በማሳወቅ ኢንስቲትዩቱ መልስ ይጠብቃል ብለዋል አቶ መስፍን።

የፈተናውን ቀን የተወሰነው በተቋማቱ የጋራ ውይይት መሆኑን የገለፁት አቶ መስፍን ቀኑ መስተካከል ካለበትም እነርሱን በማነጋገር ይሆናል፡፡ አለዚያ ግን ኢንስቲትዩት በራሱ ስልጣን የፈተናውን ቀን የሚቀይርበት ሁኔታ የለም በማለት ተናግረዋል፡፡

አቶ መስፍን እንደሚሉት ተማሪዎቹ አሁንም ቢሆን ምንም አይነት የመርሀ ግብር ለውጥ እንደሌለ መገንዘብ አለባቸው፡፡ እየሰራን የምንገኘው በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ነው፡፡ ፈተናው በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ይሰጥ አይሰጥ የሚለውን ጉዳይ የሚወስነው በሚቀጥለው ሳምንት የሚደረገው አጠቃላይ ስብሰባ ውሳኔ ይሆናልም ብለዋል፡፡

በደረሰ አማረ
ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *