በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ በህገ-ወጥ መንገድ የሰፈሩ ከአንድ ሽህ በላይ አባወራዎችን ከፓርኩ እንደሚያስወጣ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ እንደተናገሩት፣በአሁኑ ወቅት በፓርኩ ዉስጥ አንድ ሽህ 80 አባወራዎች በህገ-ወጥ መንገድ ሰፍረዉ ሲገኙ ከ100 ሽህ በላይ የቁም እንስሳት አሏቸዉ፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት የፓርኩን ደህንነት ለማረጋገጥ ከእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎችና ከአካባቢዉ ማህበረሰብ ጋር በመነጋገር እንዲወጡ ማድረግ ቀዳሚዉ ምርጫ መሆኑን ባለስልጣኑ እንደሚያምን ተናግረዋል፡፡

ይህ ሲሆን ግን በፓርኩ ዉስጥ የሚያገኙትን ተጠቃሚነት ሲወጡም እንዲያገኙ ለማድረግ የተቀናጀ ስራን እንደሚጠይቅም አልሸሸጉም፡፡

ብሔራዊ ፓርኩ በ1966 ዓ.ም ሲቋቋም ከቦታዉ እንዲወጡ የተደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በ1967 እና በ1983 ዓ.ም የነበሩ የሽግግር ወቅቶችን ተጠቅመዉ ወደ ፓርኩ ዘልቀዉ ገብተዉ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ አሁንም ተመሳሳይ ድርጊት ነዉ የተፈጸመዉ ብለዋል፡፡

ከዚህ ዉጭ ግን እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ከሁለት ዓመት ወዲህ እንዲገቡ የተደረጉ ናቸዉ በሚልና ሌላ መልክ ለማስያዝ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚለቀቁ መረጃዎች ፍጹም ከእዉነት የራቁ ናቸዉ ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡

አሁንም ቢሆን በፓርኩ ዉስጥ የሚገኙ ህብረተሰብ ክፍሎችን አወያይቶና አሳምኖ ካልሆነ በስተቀር ጫና በመፍጠርና በማስገደድ የሚመጡ መፍትሄዎች ዘላቂ እና አወንታዊ ለዉጥ ያመጣል ብሎ ተቋሙ እንደማያምንም ገልጸዋል፡፡

በሙሉቀን አሰፋ
ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *