የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ ያስተላለፉትን ንግግር ተቃወመች።

ቤተክርስቲየኗ ዛሬ በሰጠችው መግለጫ ሕዝባችን በዚህ ተስፋ ውስጥ በገንዘቡም በጉልበቱም በሙያውም የበኩሉን ድጋፍ እየተረባረበ ባለበት ወቅት ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በአገራችን ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ግድባችንን አስመልክቶ አገራትን ወደ ግጭትና አለመግባባት ውስጥ የሚከት የጥፋት መልዕክት ማስተላለፋቸው እንዳሳዘናት አስታውቃለች።

ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ ታፍራና ተከብራ የኖረችውና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ምሳሌ የሆነችው አገሪቱ አገረ እግዚአብሔር ሕዝቡ ሕዝበ እግዚአብሔር በመሆኑና በዚህም የሰውና የእግዚአብሔር አንድነት አገራችን በእግዚአብሔር ተጠብቃ የኖረች አገር በመሆኗ ነውም ብላለች ቤተክርስቲያኗ ባወጣችው መግለጫ፡፡

ከዚህም ጋር በዘመናት አገሪቱን እንዲመሩ የተጠሩ መሪዎችና ሕዝቧ በአገራችን ላይ ይነሳሱ የነበሩ ወራሪዎች ያሰቡት ሳይሳካላቸው አገሪቱ ድንበሯ ከነክብሯ ተጠብቆ የኖረችና የሕዝባችን አገራዊ አንድነት ተጠብቆ የኖረ በመሆኑ ነውም ብላለች።

ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ሆነ ከከሌሎች ተመሳሳይ አካላት በአገራችን ላይ እየተላለፈ ያለው የጥፋት ጥሪ መተዛዘቢያ ከሚሆን በስተቀር አገራችን ጠባቂዋ በሆነው እግዚአብሔርና በሕዝባችን አንድነት ተከብራና ተጠብቃ እንደምትኖር ሙሉ እምነቷ መሆኑን በመግለጫዋ ጠቁማለች።

ኢትዮጵያ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ያላነሱ ልጆቿ እንደየአካባቢያቸውና እንደ አደጉበት አካባቢ የተለያዩ ቋንቋ እየተናገሩ ባሕላቸውንና ሥርዓታቸውን ጠብቀው በመከባበርና በአንድነት መንፈስ እየተረዳዱ የሚኖሩበት እንግዳ በመቀበልና ቤት ያፈራውን ተካፍሎ በመኖር የሕዝባችን ልዩ መታወቂያው እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ቤተክርስቲያኗ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአገራችን ላይ ያስተላለፉት የጦርነት ጥሪ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ እንደምትቃወም አስታውቃለች።

መላውም የዓለም መንግሥታትና ሕብረተሰብ ችግሩን በጥልቀት እንዲገነዘቡትም ቤተክርስቲያኗ አሳስባለች።

በአገር ውስጥ ሆነ ከአገር ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ፣ የፌዴራልና የክልል መሪዎች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የትኛውንም የየግልና የቡድን አመለካከታችንን ወደጐን በመተው አንድነታችንን ልናጠናክርበት የሚገባ ወቅት መሆኑን በመገንዘብ ኢትዮጵያዊ አንድነታችሁን ከምንጊዜውም የበለጠ ጠብቃችሁ ለአገራችን ሕልውና እንዲቆሙ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያዊያን
ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *