የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለሰባት የጤና ተቋማት ወደ ውጭ አገራት ለሚጓዙ መንገደኞች የኮሮና ቫይረስ ምርምራ እንዲያደርጉ ፈቀደ።

የግል የኮሮና ቫይረስ የምርመራ ማዕከላት እንደ ልብ አለመገኘት በርከት ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ቅሬታ ሲያስነሳ ቆይቷል፡፡

በተለይም የዉጭ ጉዞ ያለባቸዉ ሰዎች አብዝተዉ ሲያማርሩ ቆይተዋል፡፡

የምርመራ ዉጤት ማፍጠኛ ገንዘብ መጠየቃቸውንም መንገደኞቹ ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡

አሁን ላይ ታዲያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቀደም ሲል ምርመራ ሲያደርግ የነበረዉን ኢንተር ናሽናል ክሊኒካል ላብራቶሪስን ጨምሮ 7 የግል ሆስፒታሎች የኮቪድ 19 ምርመራ እንዲያደርጉ ፈቅጃለሁ ብሏል፡፡

ይህንም የሚመለከታቸዉ አካላት ሁሉ እንዲያዉቁት ተደርጓል ብለዋል፤ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብሄራዊ የኮቪድ-19 ላብራቶሪ ክፍል አስተባባሪ አቶ ይማም ጌታነህ፡፡

የኮቪድ ምርመራ እንዲያደርጉ የተፈቀደላቸዉ ሆስፒታሎችም፣አሜን ጠቅላላ ሆስፒታል፣አሜሪካ ሜድካል ሴንተር፣ቤተ-ዛታ ሆስፒታል፣ኢንተር ናሽናል ክሊኒካል ላብራቶሪስ፣ አዲስ አበባ ሲልክ ሮድ ሆስፒታል፣
ኢንተርናሽናል ኦርጋናይዛሽን ፎር ማይግሬሽን እና ዉዳሴ ዲያግኖስቲክስ መሆናቸዉ ተገልጿል፡፡

ይህም የተሻለ አገልግሎት የመስጠት ዉድድርን ፈጥሮ ቀደም ሲል ሲነሳ የነበረዉን የዉጤት መዘግየት ያቃልላል ብለዋል አቶ ይማም፡፡

ሆስፒታሎቹ የተመረጡትም ባላቸዉ የላብራቶሪ ጥራት፣የሰለጠነ የሰዉ ሃይልና አጠቃላይ አቅምን መሰረት ባደረገ መልኩ መሆኑንም ነዉ አቶ ይማም የነገሩን፡፡

የሚያስከፍሉት የዋጋ መጠንም ቢሆን ዉድድሩ በራሱ እንዲያሻሽሉ ያደርጋቸዋል፤ ከዛ ባለፈ ግን ሁለቱንም ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለኮቪድ 19 ምርመራ ምን ያህል ማስከፈል እንዳለባቸዉ የሚወሰን መሆኑንም የላብራቶሪ ክፍል አስተባባሪዉ ጨምረዉ ገልጸዋል፡፡

አሁንም ተመሳሳይ አገልግሎት ለመስጠት በሂደት ላይ ያሉ ሆስፒታሎች መኖራቸዉንና በቅርቡም ቁጥራቸዉ እስከ 22 እንደሚደርሱ ሰምተናል፡፡

በዚህ ወቅትም ጉዞ ያለባቸዉ ብቻም ሳይሆን በራሳቸዉ ለመመርመር የሚፈልጉ ሰዎች ቢበራከቱ ለማስተናገድ አቅም ይፈጥራል ተብሏል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሙሉቀን አሰፋ
ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *