በገና ዋዜማ እና በዓል ዕለት ድንገተኛ የእሳት አደጋዎች ቢከሰቱ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ድንገተኛ የእሳት አደጋዎች ቢከሰቱ ምላሽ ለመስጠት በሶስት ፈረቃ እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽኑ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግሯል፡፡

ተቋሙ በመጪው የገና በዓል እና ዋዜማ ድንገተኛ አደጋዎች ቢከሰቱ ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ እንዲረዳ በማሰብ በሶስት ፈረቃ የአደጋ መከላከል ስራውን ለ24 ሰዓታት በመስራት ላይ እንደሆነ የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ ተናግረዋል፡፡

አደጋ የመከላከል ስራው ከህዳር 18 አስከ ጥር 15 ያለውን ጊዜ በአፅኖት ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ አውጥቶም ወደ ትግበራ መገባቱም ተገልጿል፡፡

በተያያዘም አደጋው ቢከሰት 30 የሚሆኑ የአደጋ ጊዜ ተሸከርካሪ መኪናዎች ፣ 19 አምቡላንሶች 2 ቦቲ መኪኖች፣ 6 ኮማንድ ተሸከርካሪዎች እና ሁለት ክሬኖች ዝግጁ ተደርገዋል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ከሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ውሃና ፍሳሽ ባለ ስልጣን፣ መብራት ሃይል፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሚሽን ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

ህብረተሰቡም በራሱ በኩል የሚጠበቀውን ሃላፊነት ሊወጣ ይገባል የሚሉት ሃላፊው ፤ የሃይል መጨመር እና መቀነስ በበዓላት ሰሞን ሊከሰት ስለሚችል በአንድ ማከፋፈያ ብዙ የኤሌትሪክ ሶኬቶችን ሰክቶ አለመጠቀምን ጨምሮ ሻማ አብርቶ አለመተኛት ዋናዎቹ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው የሚገቡት ናቸው ብለዋል፡፡

በተያየዘም አደጋዎች ቢያጋጥሙ በመስመር ስልክ 0111555300 ፣ 0111568601 እና 939 ላይ በመደወል አሳውቁኝ ሲል ኮሚሽኑ አሳስቧል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
ድረ ገጻችንን https://ethiofm107.com/ ይጎብኙ::

በረድዔት ገበየሁ
ታህሳስ 27 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *