የብልፅግና ፓርቲ ቀጣይ ፈተና ምን ሊሆን ይችላል?

ከህወሀት መደምሰስ በኋላ የብልጽግና ቀጣይ ፈተና ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ጥያቄ ኢትዮጵያውያን መጠየቅ የጀመሩት የአገር መከላከያ ሰራዊት መቀሌን መቆጣጠሩን የሚያበስረው ዜና ከተሰማ ሰአት አንስቶ ነው፡፡

ከዚህ የድል ዜና በኋላ ብዙዎች የዜጎች መፈናቀል እና የፖለቲካ ትኩሳት የሚፈጥራቸው አሰቃቂ ክስተቶችን ከመስማት እንገላገላለን በሚል ተስፋ አድርገው ነበር።

ለመሆኑ አገር እየመራ ያለው የቀድሞው ኢህአዴግ የአሁኑ ብልጽግና ፓርቲ ከህወሀት መደምሰስ በኋላ ፈተናዎቹ ምን ምን ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ኢትዮ ኤፍ ኤም በፖለቲካ ነክ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ በመስጠት ከሚታወቁት ዶክተር አለማየሁ አረዳ ጋር ቆይታ አደርጓል፡፡

እንደ ዶክተር አለማየሁ ገለጸ ህወሀት በአካል ቢወገድም የዘረጋው አጠቃላይ ስርአት፣አስተሳሰቡና የመንፈስ ልጆቹ የገዢው ፓርቲ ፈተና ይሆናሉ ብለዋል።
ይህ እንዳለ ሆኖ “ዋናው የብልፅግና ቀጣይ ፈተና ራሱ ብልፅግና ነው” ብለዋል ዶክተር አለማየሁ፡፡

የተወሰነ መረጃ እንዳገኘሁት ከሆነ ይላሉ ዶ/ር አለማየሁ ብልፅግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔውን አድርጎ ፕሮግራሙንና መታዳደርያ ደንቡብ አላፀደቀም፡፡
የኢህአዴግ የነበረው በሙሉ ተገልብጦ ብልፅግና እንዲባል፣ አባላቱም ልክ እንደ ጃኬት ተገልብጠው ነው የመጡት ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሚቀጥለውን ምርጫ እንዳሉ እነሱ በፌደራልም፣ በክልልም ተመርጠው ፤ ስልጣን ለመያዝ ተዘጋጅተዋል ፤ ሽንፈት የመቀበል ስነ ልቦናዊ ዝግጅቱም ያላቸው አይመስሉም ብለዋል፡፡
እነዚህ የብልፅግና ካድሬዎች ምን ያህል የጠራ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ አላቸው? ምን ያህልስ ለውጡን ተገንዝበውታል? ምን ያህልስ ለህዝቡ ተገቢ አመራር የመስጠት አቅም አላቸው?

የሚለው አጠራጣሪና ለፈተና ያልቀረበ ነው ያሉ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ስለ በጋራ ስለ መኖር፣ ስለ አንድነት፣ስለ ዴሞክራሲ፣ በጋራ ስለ መበልፀግ፣የምንሰማው ከዶ/ር አብይ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሌሎቹ ካድሬዎች ባሉበት ነው ያሉት የሚሉት ዶ/ር አለማየሁ ፤ በየክልሎቹ ያሉት የብልፅግና ቅርንጫፎች እውነት ለሌሎች ፓርቲዎች ሰፊ የመጫወቻ ሜዳ ይለቃሉ? የሚለው በጣም አጠራጣሪ ነው ብለዋል፡፡

ሌላው ይላሉ ዶ/ር አለማየሁ፤ ሌላው ትልቁ በጥበብ ሊፈታ የሚገባው ቀጣዩ የገዢው ፓርቲ ፈተና ፤ የእነ ወላቃይትና ራያ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
አካባቢዎቹ ነፃ ወጥተናል ሲሉ አውጀዋል፤ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተካሄደ ዘመቻ መሆኑ መዘንጋት የለበትም ይላሉ፡፡

ምርጫው እየቀረበ ሲሄድ ጥያቄዎቹ እየከረሩ ሲሄዱ ለመንግስትም ለድንበር ኮሚሽኑም ትልቅ አጣቢቂኝ ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡
በቃ ህወሀት ተወግዷል በሚል ከትግራይ ክልል ነጥቆ አማራ ክልል ውስጥ ማስገባት በዛ በኩል የሚያስከፋው ህዝብ ስለሚኖር ፍትሀዊ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ህወሀት ለዘመናት በቅኝ እንደያዛቸው አድርጎ ሲያስተዳድራቸው የነበረው፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት እስከ ዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈፀምባቸው የኖረውንና ማንነታችንን ተነጥቀናል፤ የሚሉትን ዜጎች በቃ እንደ ከዚህ ቀደሙ ቀጥሉ ማለትም ተገቢ አይደለም፣ህዝቡ ነቅቷል፡፡

ከዚህ በመለስ ለትግራይ፣ከዚህ በመለስ ደግሞ ለማራ ብሎ ሸንሽኖ ማከፍፈልም አይሆንም፤ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እነዚህ አካባቢዎች ኢህአዴግ ስልጣን ከመያዙ በፊት የትኛው አስተዳደር ስር ነበሩ፣ የህዝቡስ ፍላጉትና ስነ ልቦና (Psychological makeup)፣ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ለዲሞግራፊ ተብሎ ስለ ሰፈሩ ህዝቦች፤ የሚሉትና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ የአማራ ክልልና የትግራይ ክልል ፌዴሬሽን ምክር ቤትም የሚመለከተው ሁሉ ቁጭ ብለው መነጋገር አለባቸው ያሉ ሲሆን እስከ ምርጫው ግን ግዛቶቹ በፌደራል መንግስት ስር ያሉ ልዩ አስተዳደሮች ተመስርቶላቸው ነው መቆየት ያለባቸው፣ የሽግግርና ፋታ መውሰጃ ጊዜ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል ዶክተር አለማየሁ፡፡

በቅድሚያ መተማመን መፈጠር አለበት ብለዋል፡፡
ሌላው ሙሉ በሙሉ በኦነግ ሸኔ የሚላከከው፤ የመተከልና ሌሎች ኦሮሚያ ክልል ላይ በተለይ አማራ ላይ የሚፈፀሙ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፤ ራሱ ብልፅግና በተለይ ፤ የኦሮሚያ ክንፍ ሊፈተሽባቸው የሚገቡ ወንጀሎች ናቸው ብለዋል፡፡

ሸኔ ተደመሰሰ ሲባል ተማረከ ተብሎ የምንሰማው 7 ክላሽና 30 ኋላ ቀር መሳርያ ነው፤ ይሄ የሚያሳይህ ምን ያህል ደካማ ሀይል እንደሆነ ነው፤ መንግስት አቅቶት ሳይሆን ራሱ ገዢው ፓርቲ ውስጥ የሚገኙ ለኦነግ ሸኔ የሚያደሉ በልፅግና ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በቁጥር ትንሽ ስላልሆኑ ነው ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ የፖለቲካ አሰላለፍ ጥናት ይፈልጋል ያሉት ዶክተር አለማየሁ ግብፅን የመሰሉ የውጪ ሀይሎችም፤ከፍተኛ ገንዘብ የሚያፈሱበት ነው ብለዋል፡፡
ለዶ/ር አብይ መንግስት ትልቅ ራስ ምታት ቤንሻንጉል ነው የሚሉት ዶ/ር አለማየሁ አልጀዚራ ላይ አንድ የግብፅ ሰው ቤንሻንጉል የሚባል ቦታ አለ፣ በዛም መግባት እንችላለን ሲል እንደነበር አንስተዋል፡፡

በመጨረሻም ፤ ዶ/ር አለማየሁ ፤ ብልፅግና ራሱን እንዲያጸዳ ያሳሰቡ ሲሆን ፤ ግልፅ አቋምና ፍኖተ ካርታ እንጂ ለሁሉ ነገር ግብረ ሀይል አያስፈልገውም ሲሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጀመርያ ደረጃ ራሱ ብልፅግና ፓርቲ ኢህአዴግ ያለበሰውን ጥብቆ አውልቆ መለወጥ አለበት ይላሉ ዶ/ር አለማየሁ፡፡

ከስር ያለው የፓርቲው መሰረት እላይ ባለው አመራር ዝም ብሎ የሚጎተት ይመስላኛል ብለዋል፡፡
ምንድነው ግብረ ሀይል ማብዛት ሲሉ የሚጠይቁት ዶ/ር አለማየሁ ዋናው እና መሰረታዊ የሆነው የሀገራችንን ፖለቲካዊ ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት ነው ገዢው ፓርቲ መሞከር ያለበት ብለዋል፡፡

ዶ/ር አብይ የሚሰራውን አምስት በመቶ የሚሰራ ብልፅግና ውስጥ የለም ያ ሲሆን ፕሮግራሙና መተዳደርያ ደንቡ አለመፅደቁን የማያውቅ የማዕከላዊ ኮሚቴ እንዳለ አውቄያለሁ፡፡ ሌላ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ደግሞ ጸድቋል ይለኛል፡፡ ሁለቱም ደግሞ የኢህአዴግ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ነበሩ ሲሉ ትዝብታቸውን ገልፀዋል፡፡

እነዚህ ምርጫ ሲመጣ እኛ እኮ ብልፅግና ነን ወደ የትም አንሄድም ነው የሚሉን ያሉ ሲሆን ብልፅግና ቀጣዩን ፈተናውን ለመሻገር በጠራ አስተሳሰብና በጠራ ፍኖተ ካርታ መንቀሳቀስ አለበት ሲሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በሔኖክ አስራት
ጥር 5 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *