በጋምቤላ ክልል የኦነግ አባላት ናችሁ በሚል እና ህወሀትን ትረዳላችሁ በሚል የታሰሩ ዜጎች በአፋጣኝ እንዲፈቱ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አሳሰበ።


ኮሚሽኑ በጋምቤላ ክልል የእስረኞች አያያዝ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ሊሻሻል እንደሚገባም አሳስቧል።
ኮሚሽኑ ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በጋምቤላ ክልል ያለው የእስረኞች አያያዝ እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ሊረጋገጥ ይገባል ብሏል።

ኮሚሽኑ በታኅሣሥ ወር በጋምቤላ ከተማ እና በአኝዋህ ዞን በመገኘት፣በአካባቢው ስላለው የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ክትትል አድርጎ ከክልሉ ኃላፊዎች ጋር መወያየቱን ገልጿል።

ኮሚሽኑ በጎበኛቸው የክልሉ ማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች አያያዝና ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ በአፋጣኝ ሊሻሻል የሚገባው ነው።

በተለይም በኦነግ ሸኔ አባልነት ተጠርጥረው በጋምቤላ ከተማ ማረሚያ ቤት ከታኅሣሥ መግቢያ ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙ ሁለት የ 11 እና የ 12 ዓመት ሕፃናት ወንዶች፣ እንዲሁም አንድ የ14 ዓመት ሕፃን ሴት በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ አሳስቧል።

በተጠርጣሪዎች ሕፃናት ወንዶች ላይ ከፍተኛ ድብደባ ያደረሱ የፀጥታ አባላት ላይ አፋጣኝ ምርመራ በማካሄድ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድም ኮሚሽኑ ጠይቋል።
ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ሕጻናቱ በእስር ላይ መሆናቸውን ገልጿል።

በተጨማሪም “ሕወሓትን በገንዘብ እና በተለያየ መንገድ ይረዳሉ፣ በክልሉ ውስጥ በሕዝብ መካከል ግጭት የመቀስቀስ ዓላማ ይዘው ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ምክንያት፣ ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በአቦቦ ከተማ፣ በአኝዋህ ዞን ማረሚያ ቤት 20 ሰዎች፤ እንዲሁም በጋምቤላ ከተማ ማረሚያ ቤት 70 ሰዎች፣ በአጠቃላይ በአብዛኛው የትግራይ ተወላጅ የሆኑ 90 ሰዎች፣ በክልሉ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።

በኢሰመኮ ጉብኝት ወቅት፣ በእነዚህ 90 ተጠርጣሪዎች ላይ በፌዴራል ፖሊስም ሆነ በክልሉ ፖሊስ በኩል የተጀመረ የወንጀል ምርመራ ሂደት አለመኖሩ በመገለጹ፣ ኮሚሽኑ ይህንኑ አሳሳቢ ጉዳይ ለሚመለከታቸው የክልሉ ኃላፊዎች አሳውቆ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በአፋጣኝ ምርመራ እንዲጀመርና የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ አሳስቧል።

ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስም እነዚህ ዜጎች በእስር ላይ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል።
በሌላ በኩል፣ ኮሚሽኑ በጉብኝቱ ወቅት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን አነጋግሯል።
ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች ‘የምርጫ ሥነ ምግባር መግባቢያ ሰነድ’ የፈረሙ መሆናቸውን ገልጸው፣ ቢሮና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ለማግኘት፣ በክልሉ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ለመስራትና፣ የፓርቲያቸውን ዝግጅቶችን ለማድረግ እንግልት እንደሚገጥማቸውና በአንዳንድ አባላቶቻቸው ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ መድረሱን እንደገለጹለት ኮሚሽኑ በመግለጫው ጠቁሟል።

በተጨማሪም አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በተለያየ ወቅት 35 አባላቱ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ለእስር መዳረጋቸውን ገልጿል።
እንዲሁም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባል ቤተሰብ በመሆናቸው ከመንግስት ስራ የታገዱ እና ያለፈቃዳቸው ‘ለብልጽግና ፓርቲ መዋጮ’ በሚል ከደሞዛቸው ላይ የመዋጮ ክፍያ የተቆረጠባቸው ሰዎች መኖራቸውን አስረድተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በክልሉ የሚገኙ የምርጫ ወረዳ ተወካዮች ብዛት አወሳሰን ዙሪያ ያላቸውን ቅሬታ ለክልሉ ባለሥልጣናት ቢያሳውቁም፣ ምላሽ አለማግኘታቸውንም ለኮሚሽኑ አሳውቀዋል።

ኢሰመኮ በእነዚህና ሌሎችም የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ከክልሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በተወያየበት ወቅት፣ የክልሉ ኃላፊዎች ለሰብአዊ መብቶች መሻሻል በጎ ምላሽ ሰጥተው፣ በተለይም የገዢው ፓርቲ አባል ካልሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ላይ ሲሰበሰብ የነበረው የፓርቲ አባልነት ክፍያ በተመለከተ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ እንደተወሰደ ገልጸዋል።
ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያዊያን
ጥር 17 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *