ኢዜማ በቀጣዩ ምርጫ ከየትኛውም ፓርቲ ጋር ሳይዋሀድ ብቻውን በመላው የሃገሪቱ የምርጫ ወረዳዎች እንደሚወዳደር አስታወቀ።

ኢዜማ በቀጣዩ ምርጫ ከየትኛውም ፓርቲ ጋር ሳይዋሀድ ብቻውን በመላው የሃገሪቱ የምርጫ ወረዳዎች እንደሚወዳደር አስታወቀ።

የኢትዮጲያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሳወቀው ለቀጣዩ ስደስተኛ ዙር ሃገራዊ ምርጫ በመላ ሃገሪቱ 547 የምርጫ ጣቢዎች ሲኖሩ ኢዜማ በ435 የምርጫ ወረዳዎች ዕጩዎችን ያቀርባል፡፡

የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ እንደነገሩን ፓርቲያቸው በአዲሰ አበባ በሚገኙ 23 የምርጫ ወረዳዎች ለመሳተፍ ከፍተኛ ዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

ፓርቲያችን በአዲስ አበባ በሚገኙ 23 የምርጫ ጣቢዎች ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት መቀመጫዎች ይወዳደራል ብለዋል አቶ ናትናኤል፡፡

ኢዜማ ለረዥም ዓመታት በፖለቲካው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው ጉምቱ ፖለቲከኞች ያደራጁት ጠንካራ ፓርቲ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ናትናኤል ኢዜማ ድምጽ ለማግኘት ሲል ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር አይዋሃድም ብለዋል፡፡

በሃገራችን በምርጫ ሰሞን ስምምነት በማድረግ ውህደት የፈጸሙ ፓርቲዎች መጨረሻቸው መፈረካከስ ሲሆን ተመልክተናል ያሉት አቶ ናትናኤል እኛ ይህንን ታሪክ ደግመን ሰርተን አንሳሳታም ለዚህም ስንል በተደራጀ እና በተጠናከረ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው ሲሉ ነግረውናል።

ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል ነው የምናያቸው ፡፡ ከማንም ጋር ድምጽ ለማግኘት ስንልም አዲስ ስምምነት አናደርግም ብለዋል፡፡

በምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን የሚያስመዘግቡት ከየካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

ኢዜማ ግን ቀደም በማለት በፓርቲው አሰራር መሰረት ዕጩዎችን ከአባላቶቹ መካከል በመምረጥ የውስጥ ፓርቲ ቅድሚያ ውድድር በማድረግ ላይ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ናትናኤል ይህንንም እስከሚቀጥለው ሳምንት ድረስ አገባድደን በአገር አቀፍ ደረጃ በ435 የምርጫ ወረዳዎች ውስጥ ኢዜማን ወክለው የሚወዳደሩ ሰዎችን ለይተን የምናስቀምጥ እና ጊዜው ሲደርስም ማን የት እንደሚወዳደር እናሳውቃለን ብለውናል፡፡

በያይኔአበባ ሻምበል
ጥር 18 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *