በከተማዋ ቅዳሜ እና እሁድ በደረሱ አምስት ድንገተኛ የእሳት አደጋዎች ምክንያት ከ100ሚሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ነው የተገለጸው፡፡
የእሳት እና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እንዳስታወቀው በትላንትናው እለት በጉለሌ እጸዋት ማእከል የደረሰው የእሳት አደጋ ሁለት ሄክታር ቦታ የሸፈነ ነበር ብሏል፡፡
በዚህ አደጋ የተነሳም ከ200 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት ለውድመት መዳረጉ ተነግሯል፡፡
እንደዚሁም ምን ያህል ንብረት ደግሞ ከውድመት እንደተረፈ ለጊዜው አልታወቀም ተብሏል፡፡
የእሳት አደጋው ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር 135 ሺህ ሊትር ውሀ ለአገልግሎት ላይ ውሏል ሲል ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ጽዮን ሆቴል አካባቢ በአንድ ሼድ ላይ በደረሰው የእሳት አዳጋ ከ50 ሺህ ብር በላይ የሚጠጋ ንብረት ለውድመት ሲዳረግ ከ4 ሚሊየን ብር በላይ የሚጠጋ ንብረት ደግሞ ማዳን ተችሏል፡፡
እንደዚሁም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ኮሎምብያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመኖርያ ቤት ላይ የደረሰ አደጋ ነው፡፡
በአደጋው 20 ሺህ ብር በሚገመት ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ከ300 ሺህ ብር በላይ በሚገመት ንብረት ደግሞ ማዳን ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ገርጂ ማርያም አካባቢ ላይ በአንድ ህንጻ ላይ የደረሰ የእሳት አደጋ ነው፡፡
በዚህኛው የእሳት አደጋ ከ100 ሺህ ብር በሚጠጋ ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን በተደረገው ብርቱ ስራ ከ100ሚሊየን ብር በላይ ከውድመት ማዳን እንደተቻለ ነው የተገለጸው፡፡
ሌላኛው የእሳት አደጋ የደረሰው ደግሞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ እንጦጦ ማርያም አካባቢ ላይ በሚገኝ የእንጨት ክምር ላይ የደረሰ አደጋ ነው፡፡
በተደረገው ብርቱ ርብርብ ወደ አንድ ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን የተቻለ ሲሆን ሶስት መቶ ሺህ የሚጠጋ ንብረት ደግሞ ለውድመት መዳረጉንም ተገልጻል፡፡
በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 10 እፎይታ የገበያ ማዕከል ላይ በሚገኙ ሱቆች ላይ የተከሰተው የእሳት አደጋ አሁን ላይ በቁጥጥር ስር ውሏል ተብላል፡፡
በዚህ አደጋ ምክንያት የደረሰው የጉዳት መጠን ደግሞ በማጣራት ላይ እንደሚገኝ የእሳት እና የአዳጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግኑኝነት ሀላፊ አቶ ጉልላት ጌታነህ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ጥር 24 ቀን 2013 ዓ.ም
