የጡረታ መዋጮ ገቢ የማያደርጉ የግል ድርጅቶች ንብረታቸውን እስከመሸጥ የሚደረስ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል ተባለ።


ድርጅታቸውን ማዘጋትና ንብረታቸውን እስከማሸጥ እርምጃ እንወስዳለን ሲል አስታወቀ፡፡

የፌደራል የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የጡረታ መዋጮ ሰብስበው ገቢ የማያደርጉ ድርጅቶች እንዳሉ አስታውቋል።

ኤጀንሲው እንዳስታወቀው ከቀጠሯቸው ሰራተኞች የጡረታ መዋጮ ሰብስበው ገቢ የማያደርጉ ፈጽሞ ሰራተኞቻቸውንም በኤጀንሲው የማያስመዘግቡና የጡረታ መዋጮ ሰብስበው በተገቢው ጊዜ ገቢ የማያደርጉ ድርጅቶች ፈተና ሆነውብኛል ብሏል፡፡

የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ታረቀኝ ማሞ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት በ2003 ዓ.ም በአዋጅ የተቋቋመው ኤጀንሲው 206 ሺ ድርጅቶችን መዝግቧል።

ኤጀንሲው ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ እስከ መስከረም 2013 ዓ.ም ድረስ 46.6 ቢሊየን ብር የጡረታ መዋጮ ገቢ መሰብሰቡን ተናግሯል።

የፌደራል የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ፈተና የሆኑበትን ጉዳዮች ለመፍታት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሆነና እንደሚወስድም አስታውቋል።

በወቅቱ የጡረታ መዋጮ ገቢ የማያደርጉ ድርጅቶችን በወለድ እንዲከፍሉ የማድረግ አለፍ ካለም ድርጅታቸውን ማዘጋትና ንብረታቸውን እስከማሸጥ እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል አቶ ታረቀኝ
ከዚህ ሁሉ በፊት ግን ድርጅቶች ዕዳ ውስጥ ሳይሆኑ ተገቢውን የጡረታ መዋጮ እንዲከፍሉ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አሳስበዋል።

የፌደራል የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ መገናኛ አካባቢ ያስገነባውን ባለ 15 ወለል ህንጻ በቅርቡ እንደሚያስመርቅ ሰምተናል፡፡

በመቅደላዊት ደረጀ
የካቲት 4 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *