ኦነግ በቀጣዩ ምርጫ ላይ የሚያስመዘግበው እጩ ተወዳዳሪ እንደሌለው አስታወቀ።

ከአራት ወራት በኋላ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ፓርቲዎች የእጩ ተወዳዳሪዎቻቸውን ከሰኞ ከየካቲት 8 እስከ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ማስመዝገብ እንዳለባቸው የምርጫ ቦርድ ጊዜ ሰሌዳ ያስረዳል።

በውዝግብ ውስጥ የሚገኘው ኦነግ ደግሞ የውስጥ ችግሩን ሳይፈታ የእጩ ምዝገባ ወቅት ደርሷል።

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ቀናት በቀሩት የእጩዎች ምዝገባ የማስመዘግበው እጩ እንደሌለው ገልጿል።

ፓርቲው እንዳስታወቀው ከሆነ በየምርጫ ክልሎች ላስመዘግባቸው ያሰብኳቸው እጩ ተወዳዳሪዎቼ በሙሉ በእስር ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡

ምርጫ ስለመካሄዱ በራሱ እርግጠኛ አይደለሁም የሚለው ኦነግ በፖርቲያችን ላይ ከፍተኛ ጫና ከገዢው ፖርቲ እየደረሰበት እንደሆነ ተናግሯል።

የፖርቲው ቃል አቀባይ አቶ በቴ ኡርጌሳ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት አስፈላጊ የሚባሉ የምርጫ ዝግጅቶችን ተንቀሳቅሰው ማከናወን እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ኦነግ የገጠመው ውስጣዊ መፈረካከስም በራሱ በብልጽግና ፓርቲ ጣልቃ ገብነት የተፈጸመ ነው የሚል ዕምነት እንዳላቸውም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

ብልፅግና የራሱን ከፍተኛ አባላት ከማዕከላዊ አባልነት ሲያግድ ማንም በጸጋ ነው የተቀበለው እኛ በፖርቲያችን ውስጥ ያንን ውሳኔ ስንሰጥ ግን ማንም ሊያከብርልን አልቻለም ብለዋል፡፡

ይህም ፓርቲያችን አላስፈላጊ ችግር ውስጥ ለመግባቱ ዋናው ምክንያት መሆኑን አቶ በቴ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ጦር ሀይሎች የሚገኘው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሜቲ ፅህፈት ቤት በፖሊስ መጠበቅ ከጀመረ ስድስት ወራት እንዳለፈውም ነግረውናል።

በዚህ ሁኔታ ስራችንን መስራት አንችልም በአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የፖርቲው ሀላፊዎችና አባላት እየታሰሩ የምናስመዘግበው እጩ የለንም ብለዋል።

እጩ ካላስመዘገባችሁ በምርጫው ላትወዳደሩ ትችላላችሁ? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ግን እኛ ምርጫ አንሳተፍም አላልንም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ምክትል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግዛቸው ገቢሳ ኦነግ ባነሳው ጥያቄ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን ጠይቀናል።

እሳቸው እንዳሉትም ታሰሩ የተባሉት ሰዎች እንደ ግለሰብ በሰሩት ወንጀል ተጠርጥረው አንጂ በኦነግ አባልነታቸው አይደለም ብለዋል።

ማንም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው ያሉት አቶ ግዛቸው ከቀበሌ ጀምሮ ያሉ 646 የብልጽግና አመራሮች ህግ በመተላለፋቸው ታስረዋል ብለዋል።

ከምርጫ ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ክልል የሚወዳደሩ ሁሉም ፓርቲዎች ጽህፈት ቤታቸውን ከፍተው እየተንቀሳቀሱ ነው የክልሉ መንግስትም ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

በያይኔአበባ ሻምበል
የካቲት 5 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *