በኦሮሚያ ክልል ኤች አይ ቪ ኤድስን ራስን በራስ መመርመር ተጀመረ።

በሙከራ ደረጃ የነበረው የኤች አይ ቪ ተመርማሪውን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ይጨምረዋል የተባለው ፤ ራስን በራስ ኤች አይ ቪ የመመርመር አሰራር ተግባራዊ መደረጉን ሰምተናል፡፡

የተናቀናጀ የጤናና የልማት አገልግሎት ድርጅት የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከኦሮሚያ ጤና ቢሮ ጋር በጋራ ለሶስት አመታት በሚተገብሩት የ400 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት በተለይ ለኤች አይ ቪ ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ይውላል ተብሏል፡፡

የፕሮጀክቱ ሀላፊ ዶ/ር ግርማቸው ማሞ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ኤች አይ ቪ ኤድስ የመመርመርያ ኪቱን ወደ ቤት ወስዶ ራስ በራስ መመርመር ፤ኤች አይ ቪ የሚመረመረውን ሰው ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ይጨምረዋል ብለዋል፡፡

ይሄ ራስን በራስ የመመርመር አሰራር በሌላ ሀገር ተሞክሮ ከፍተኛ ውጤት አምጥቷል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ሰዎች ራሳችውን እንዲያውቁ አማራጮችን የማስፋትን አስፈላጊነት ዶ/ር ግርማቸውም አፅንኦት የሰጡበት ሲሆን ይሄ ፕሮጀክት ቤተሰብና ማህበረሰብ ተኮር ነው ብለዋል፡፡

ራሱን ህብረተሰቡን በህክምና አሰጣጥ ሂደቱ ዋና ተዋናይ የማድረግ መንገድ ይከተላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ ክልል በ41 ወረዳዎች እና ከተሞች ላይ እንደሚተገበርም ሰምተናል፡፡

ኤች አይ ቪ ኤድስ በኢትዮጵያ በ5 ክልሎች እና በ2 የከተማ አስተዳድሮች በወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የፌዴራል የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በሔኖክ አስራት
የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *