በዛሬዉ እለት ቁጥራቸው 100 የሚጠጉ አሽከርካሪዎች ስራችንን አቁመናል አሉ፡፡

በመዲናዋ በታክሲ ስራ ላይ የተሰማሩ ቁጥራቸው 100 የሚደርሱ አሽከርካሪዎች ታርጋችን እና መንጃ ፍቃዳችን ተወስዶብናል በማለት ስራቸውን ከስራ ዉጭ መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡

ቁጥራቸው 100 የሚደርሱ በተለይም መስመራቸው ወደ ሽሮሜዳ አካባቢ የሆኑ አሽከርካሪዎች አድማ አድርጋችኋል በሚል መንጃ ፍቃዳችን እና ታርጋችን ተወስዶብናል፤ አሁን ላይ ስራ መስራት አልቻልንም ሲሉ ቅሬታቸውን ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አረጋዊ ማሩ እንደተናገሩት፣ ከትራንስፖርት ጋር በተያያዘ ያለው ችግር አሽከርካሪዎች ስራቸውን እየሰሩ ነው ቅሬታቸውን ማቅረብ ያለባቸው ብለዋል፡፡

እስካሁን ጥያቄዎች እየቀረቡ ያሉት በአሽከርካሪ በኩል እንጂ በማህበራት አይደለም ይህ ደግሞ አግባብነት የለውም ብለዉናል አቶ አረጋዊ፡፡

በትላንትናው እለትም ከሁለቱም ምክትል ከንቲባዎች ጋር የታክሲ ማህበራት እና ትራንስፖርት ቢሮው በጋራ ለመስራት እና ችግሩን ለመቅረፍ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ነው አቶ አረጋዊ የነገሩን፡፡

የትራንስፖርት ጉዳይ ለአዲስ አበባ ፈታኝ የሆነ ጉዳይ ቢሆንም ከሰሞኑ ደግሞ የተፈጠረው የትራንስፖርት እጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ አስቸጋሪ እንደሆነ የከተማዋ ነዋሪዎች እየተናገሩ ነዉ፡፡

ለትራንስፖርት እጥረቱ እንደ ምክንያት የሚነሳው ነገር የነዳጅ እጥረት እና የነዳጅ ዋጋ መናር ቢሆንም በአሽከርካሪዎችና እና በመንገድ ትራንስፖርት በኩል ያለው አለመግባባት ደግሞ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ እያደረገ ይገኛል ተብሏል፡፡

ያሳለፍነው ሰኞ ተወሰኑ አሽከርካሪዎች ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የስራ ማቆም አድማ አድርገዉ ነበር፡፡

ይህንንም ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ የስራ ማቆም አድማ ባደረጉ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱም አይዘነጋም፡፡

ይህ ጉዳይ አሁንም ሳይቀረፍ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ተጽእኖ እየፈጠረ ሲሆን በዚህ መካከል ህብረተሰቡ ለትራንስፖርት ችግር እየተዳረገ ይገኛል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
በሄኖክ ወ/ገብርኤል
መጋቢት 08 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *