ኢሰመኮ በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ተፈጽሟል ስለተባለዉ የሰብአዊ መብት ጥሰት በመጀመሪያ ሪፖርቱ ምን አለ?

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ተፈጽሟል ስለተባለዉ የሰብአዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ የመጀመሪያ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡

ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በትግራይ ክልል፤ በአክሱም ከተማ የተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በአጠቃላይ በክልሉ የተሟላ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊነትን የሚያመለክት ሆኖ አግኝቸዋለሁ ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በክልሉ አክሱም ከተማ የደረሰዉን የሰብአዊ መብት ጥሰትና በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ ያዉጣዉ የመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) ሪፖርቱን ሙሉዉ እንደሚከተለዉ ነዉ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
መጋቢት 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ትግራይ ክልል፤ በአክሱም ከተማ የተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በአጠቃላይ በክልሉ የተሟላ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊነትን ያመለክታል፡፡

በአክሱም ከተማ፣ ትግራይ ክልል የደረሰውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ የመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) ሪፖርቱን ይፋ አደረገ፡፡

ከበርካታ ሳምንታት ጥረት በኋላ የምርመራ ባለሞያዎቹን ወደ አክሱም ከተማ መላክ መቻሉን የገለጸው ኢሰመኮ፣ ባለሞያዎቹ ከየካቲት 20 እስከ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በከተማዋ በመቆየት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን፣ 45 የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የዓይን ምስክሮችን እና የሃይማኖት መሪዎችን አነጋግሯል እንዲሁም 20 ሰዎች የተሳተፉበት የቡድን ውይይት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር አድርጓል።

በተጨማሪም ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከአክሱም ቅድስት ማርያም ሆስፒታል፣ ከአክሱም ሪፈራል ሆስፒታል፣ ከሚመለከታቸው የቀበሌ መስተዳደር አካላት እንዲሁም ከሃይማኖት ተቋማት አገልጋዮች የተለያዩ የምስል፣ የድምጽ እና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን አሰባስቧል ።

ኮሚሽኑ በዚህ ምርመራው ያሰባሰባቸው መረጃዎችና በተለይም ከኅዳር 19 እስከ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በነበሩት ሁለት ቀናት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደተፈጸመና፤ የአክሱም ከተማ እና አከባቢው ነዋሪዎች፣ ከተለያዩ የትግራይ አከባቢዎች ጦርነት ሸሽተው በከተማዋ የተጠለሉ ተፈናቃዮችና እንዲሁም የኅዳር ፅዮን ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ለማክበር ከተለያየ ቦታዎች የመጡ ሰዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከአንድ መቶ በላይ ሲቪል ሰዎች በወቅቱ በአክሱም ከተማ በነበሩ የኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል።

በዚህ የቀዳሚ (መጀመሪያ ደረጃ) ሪፖርት የተጠቀሱ አኃዞች አጠቃላይ የተጎጂዎችን ቁጥር የሚያመላክቱ ሳይሆን፣ ኮሚሽኑ እስከዚህ ምርመራና ሪፖርት ወቅት ድረስ ብቻ ለማረጋገጥ የቻለውን የሲቪል ሰዎች ጉዳት የሚጠቁም ነው።

ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ፣ የተጎጂ ቤተሰቦች እና የአይን እማኞች በርካታ ሲቪል ሰዎች ልጆቻቸው፣ ሚስቶቻቸው እና እናቶቻቸው ፊት ጭምር በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉ አስረድተዋል።

ይህ በወቅቱ በአክሱም ከተማ በነበሩት የኤርትራ ወታደሮች የተፈጸመው መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተራ ወንጀል ሳይሆን በዓለምአቀፍ ድንጋጌዎችና መርኆች የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የሚጥስ፣ በግጭቱ ተሳታፊ ያልነበሩ ሲቪል ሰዎች ላይ ጭምር ሆነ ተብሎ ያነጣጠረ እና በሚሊተሪ አስፈላጊነት ሊገመገሙ የማይችሉ እና ሆነ ተብሎ የተደረጉ በሲቪል ሰዎች ንብረቶች በሃይማኖት ተቋማትና በሆስፒታሎች ጭምር ዝርፊያና ጉዳት ያደረሰ በመሆኑ፤ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቱ ምናልባት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ወይም የጦር ወንጀል ሊሆን ስለሚችል፤ በአጠቃላይ በክልሉ የተሟላ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ምርመራ ስራ ማካሄድ ያስፈልጋል።

የሰዓት እላፊ ገደብን ለማስከበርና በደኅንነት አጠባበቅ ምክንያት በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች የሚወሰደው እርምጃ ለሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉድለት መድረስ ምክንያት መሆኑ እጅግ አሳሳቢ መሆኑንና፤ የሰዓት እላፊ ገደብን ተላልፎ የተገኘ ሰውንም ቢሆን በተመጣጣኝ ኃይል በቁጥጥር ስር ማዋል ስለሚቻል፤ ለነገሩ ሁኔታ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል በመጠቀም የተወሰዱት እርምጃዎችና በዚህ መልክ የተገደሉ ሰዎች ሁኔታ በተሟላው ሪፖርት የጸጥታ ኃይሉንም ምላሽ በማካተት የሚጣራ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በሲቪል ነዋሪዎች ደኅንነት አጠባበቅ ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል አጠቃቀም በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባ ሪፖርቱ ያመለክታል።

‹‹በትግራይ ክልል የተከሰተውን አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በአለም ዓቀፉ የሰብአዊ መብቶች ድርጅትና በኮሚሽኑ የጣምራ ምርመራ ቡድን (joint investigation team) አማካኝነት እንዲጣራ የፌዴራሉ መንግስት ስምምነቱን ማሳወቁ ትክክለኛ እርምጃ ነው›› በማለት የገለጹት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አክለውም ‹‹አብዛኛው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባሎች በሕይወት መስዋእትነት ጭምር አገራቸውንና ሕዝብን የሚያገለግሉ ቢሆንም፤ በተወሰኑ የሠራዊቱ አባሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ለጣምራ ምርመራ ቡድኑ (joint investigation team) የሰብአዊ መብቶች ምርመራ ስራ ተገቢውን እገዛ ማድረግ ይገባል›› ብለዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያዊያን
መጋቢት 15 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *