መረጃዎች ለዓይነ ስዉራን ተደራሽ ለማድረግ ለሚሰራ ስራ አስፈላጊዉ ድጋፍ እየተደረገ አይደለም…..ፊዮሪ ፈትል የብሬል ጋዜጣ

ፈትል የመጀመሪያው የብሬል ጋዜጣ በ2013 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ ነበር መታተም የጀመረዉ፡፡

አሁን ላይ 26ተኛ እትም ላይ የደረሰው ፈትል የብሬል ጋዜጣ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ድጋፍ አለማድረጋቸው ጋዜጣዋን ተደራሽ ለማድረግ ፈታኝ እንደሆነባት የጋዜጣዋ መስራችና ባለቤት ጋዜጠኛ ፊዮሪ ተወልደ ተናግራለች፡፡

የመንግስትና ሌሎች አካላት ድጋፍ ባለመኖሩም ጋዜጣውን ከአዲስ አበባ ውጪ ማዳረስ እንዳልተቻለም ገልጻለች፡፡

4 ኪሎ አካባቢ ጉዳት አልባ የሆነው የማህበረሰብ ክፍል ጋዜጦችንና የስራ ማስታወቂያዎችን ሲያነብና ሲያይ ጉዳት ያለባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በተለይ ለዓይነ ስውራኑና ማየትም መስማትም ለማይችሉስ ብላ በማሰብ ይህን ሀሳብ ወደ ስራ እንዳስገባችም ፊዮሪ አስታውቃለች፡፡

ፈትል የብሬል ጋዜጣ በኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ማህበር የኢትዮጵያ ማይትና መስማት የተሳናቸው ማህበር የሚገኝ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ሳምንታዊው ፈትል የብሬል ጋዜጣ ከዜና ፈትል፣ ተምሳሌት ፈትል፣ ነቃሽ ብሎ ከሚያሳትማቸው አምዶች በተጨማሪ ለየት የሚያደርገውን ፈትል ልጆች ጀምሮ ዓይነ-ስውራን ለሆኑ ልጆች ተረቶችን በማቅረብ ጥሩ ዜጋን ለመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝም ነዉ የተገለጸዉ፡፡

አሁን ላይ ጋዜጣዋን ተደራሽ ለማድረግ የደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ ፈትል የብሬል ጋዜጣን ሊጀመር መሆኑ ታዉቋል፡፡

ፈትል የብሬል ጋዜጣ መስራችና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ፊዮሪ ተወልደ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳለችዉ በቅርቡ ከደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት ተስማምታለች፡፡

ይህም ዩኒቨርሲቲው በግቢው ለሚገኙና በአካባቢው ላሉ ዓይነ-ስውራን ጋዜጣዋን ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ነዉ የተባለዉ፡፡

በቀጣይ ከደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ ከሌሎች ጋርም ለመስራት ሙከራዎችን እያደረገች መሆኑን የገለጸችዉ ፊዮሪ፣ይህ ስራ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተዉ ባለመሆኑ ሁሉም የተቻለዉን ድጋፍ በማድረግ ዓይነ-ስዉራን እንደማንኛዉም የህብረተሰብ ክፍል መረጃዎችን የሚያገኙባቸዉ መንገዶች ሊመቻቹ እንደሚገባ ጠቁማለች፡፡

በመቅደላዊት ደረጀ
መጋቢት 22 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *