በሙርሌ ጎሳዎች ታፍነው የተወሰዱ ህፃናት እንዲመለሱ ተጠየቀ፡፡

ከጋምቤላ ክልል በተለያዩ ጊዜያት በሙርሌ ጎሳዎች አማካኝት እስካሁን ከ 60 በላይ ህፃናት ታፍነው ተወስደዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን የሚገኙ የሙርሌ ጎሳዎች በህገወጥ መንገድ የኢትዮጲያ ድንበርን ጥሰው በመግባት በሚፈፅሙት ህፃናትንና ሴቶችን በህገወጥ መንገድ የመጥለፍ ተግባር እስካሁን ከ 60 በላይ ሴቶችና ህፃናት ታግተው መወሰዳቸውን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ም/ሃላፊ አቶ ኦቶው ኦኮት ለኢትዮ ኤፍኤም ተናግረዋል፡፡

ከጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ጋር በምትዋሰነው ደቡብ ሱዳን በሚገኙ የሙርሌ ጎሳዎች አማካኝነት ከክልሉ በርካታ ህፃናት ታፍነው እንደተወሰዱ የነገሩን አቶ ኦቶው፣ ምንም እንኳን በሙርሌ ጎሳዎች አማካኝነት በተለያዩ ጊዜያት የተወሰዱ ህፃናት ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ቢሆንም፣ አሁንም በሙርሌ ጎሳዎች አማካኝነት በህገ ወጥ መንገድ ተወስደው የቀሩ ህፃናት በደብብ ሱዳን ይገኛሉ ተብሏል፡፡

እነዚህን ህፃናት ለማስመለስ ለምን እስካሁን እንዳልተቻለና በህገወጥ መንገድ ታፍነው የተወሰዱ ህፃናትም ሆኑ ሴቶች ወደ ቀደመ መኖሪያቸው እንዲመለሱ የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት በምክር ቤቱ አባላት ተጠይቋል፡፡

በዚህም በክልሉ በሚገኙት በአኝዋ ዞንና በንዌር ዞር ከሚገኙ ወረዳዎች የተወሰዱትን ህፃናት በሰላማዊ መንገድ ለማስመለስ ጥረት እንደሚደረግ ሃላፊው ነግረውናል፡፡

በዚህም ከቀናት በኋላ ሶስት ህፃናትንና ሁለት አዋቂ ሴቶችን ለማስመለስ ከስምምነት ላይ መደረሱን እና በቀናት ውስጥም ወደ ቀያቸው እንደሚመለሱ ጠቁመዋል፡፡

ይህን ሁኔታ ለመከላከልም ሆነ ይህ ተግባር እንዳይከሰት በክልሉ በኩል የሚሊሻና የፀጥታ ሃይልን የማደራጀት ስራ በመስራት ላይ መሆኑንና የደቡብ ሱዳን መንግስት በአጎራባች ዞኖች ላይ በተለይም በድንበር አካባቢ ያለውን ሁኔታ እንዲቆጣጠር በመነጋገር ላይ እንገኛለን ብለውናል፡፡

በቀጣይም የኢትዮጲያና የደቡብ ሱዳን መንግስት የጋራ የድንበር ኮሚሽን እንዲጠናከርና መስራትና ይህንኑ ድንበር ጥሰው የሚገቡ ህገ-ወጥ ዝውውር የሚያደርጉ የታጠቁ ሃይሎች እና ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችን እንቅስቃሴ ለማስቆም በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በየዉልሰዉ ገዝሙ
መጋቢት 22 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *